የኬንያ ፍርድ ቤት የኮቪድ ክትባት አስገዳጅ መመሪያን አገደ

እየተከተበች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያልተከተቡ ሰዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አገልግሎች እንዳያገኙ የሚከለክለውን የመንግስት መመሪያ አግዷል።

ይህ መመሪያ በሚቀጥለው ሳምንት ተግባራዊ ሊደረግ የነበረ ሲሆን ነጋዴው ኤኖክ አውራ መመሪያው ኢ-ህገ መንግሥታዊና አድሏዊ ነው በሚል ያቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የእግድ ብያኔ አስተላልፏል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አንቶኒ ሚሪማ ጉዳዩ በታህሳስ መጨረሻ እስኪታይ እና የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ብይኑ ፀንቶ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

በህዳር ወር የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ሙታይ ካግዌ መመሪያው ብዙ ኬንያውያን እንዲከተቡ ግፊት ለማድረግ ያለመ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

የኬንያ መንግሥት በአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ 10 ሚሊዮን ኬንያውያንን ለመከተብ እቅድ ይዞ ነበር።

የኮቪድ-19 የመጀመሪያውን ክትባት የተከተቡት 8.1 ሚሊዮን ኬንያውያን ሲሆኑ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሁለቱንም ክትባት ተከትበዋል።

ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ በርካታ ሆቴሎች እና የገበያ ማዕከሎች ያልተከተቡ ኬንያውያን እንዳይገቡ መከልከላቸውን ካስታወቁ ከቀናት በኋላ ነው ይህ እግድ የተላለፈው።