በአሜሪካ ከባድ አውሎ ንፋስ ባስከተለው አደጋ ቢያንስ የ70 ሰዎች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በከባድ አውሎ ነፋሶች የተመቱትን የሀገሪቱን ማእከላዊ አካባቢዎች ለመርዳት መንግሥት የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገለጹ።
በኬንታኪ በያዝነው ሳምንት አርብ ምሽት በተከሰተው የአውሎ ንፋስ አደጋ በሻማ ፋብሪካ ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጨምሮ ከ70 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንት ባይደን በአውሎ ንፋሱ የከፋ ጉዳት ለደረሰባት ኬንታኪ ፈንድ እንዲለቀቅም የፌዴራል የአደጋ ጊዜ አደጋ መግለጫ ፈርመዋል።
የአውሎ ነፋስ አደጋው በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት የከፉ መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአውሎ ንፋስ በከባድ ሁኔታ በተመታችው ሜይፊልድ ከተማ በሚገኝ ፋብሪካ ፍርስራሽ የጠፉ ሰዎችን ለማዳን ፍለጋ ላይ ናቸው።
ከፋብሪካው ፍርስራሽ ስር ከነበሩት 110 ሰዎች መካከል ከ40 በላይ ሰዎች ማትረፍ የተቻለ ሲሆን ነገር ግን የኬንታኪው ገዥ አንዲ በሼር ሌላ ሰው በህይወት ከተገኘ ተአምር ነው ብለዋል።
በአደጋው በሜይፊልድ የሚገኘው የፖሊስ ጣቢያ መውደም እና የእሳት አደጋ መከላከያ እቃዎች መበላሸት ለባለሥልጣኖቹ ፈታኝ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ተብሏል።
በግዛቱ ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መብራት እና ውሃ ተቋርጦባቸዋል።
አውሎ ንፋሱ በቀጥታ ባይመታትም ባደረሰው ከባድ ጉዳት በኢሊኖይ ውስጥ በሚገኝ የአማዞን ኩባንያ መጋዘን የነበሩ ስድስት ሰራተኞችን ጨምሮ በትንሹ 12 ሰዎች ሞተዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን የጠፉ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ማግኘት ላልቻሉ እንዲሁም እርግጠኛ መሆኑ ላልቻሉት በሙሉ በጸሎት እንደሚያስቧቸው ተናግረዋል።
"የፌደራል መንግሥት ለመርዳት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል።ይህንንን ፈታኝ ወቅት አንድ ላይ እናልፋለን" ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት የፌማ የድንገተኛ አደጋ ኤጀንሲ ሰራተኞች እሁድ እለት ወደ ኬንታኪ በመሄድ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ወይም ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ተጨማሪ መገልገያዎችን ይሰጣሉ።












