የአውስትራሊያ ቀደምት ሕዝቦችን ያኮራው የሲኒማው ቁንጮ ዴቪድ ህይወት ሲታወስ

ዴቪድ ጉልፒሊል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአውስትራሊያ ታላላቅ ተዋናዮች አንዱ የሆነው ዴቪድ ጉልፒሊል (ኪንግፊሸር) ሪድጂሚራሪል ዳላይትንግጉ ባለፈው ሳምንት በ68 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል።

ተዋናዩ በሳንባ ካንሰር ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።

በአውስትራሊያ ቀደምት ሕዝቦች (አቦርጂን) ልማድ መሰረትም ለአስከሬኑ ሽኝት ለማድረግም ወደ ትውልድ ስፍራው ተወስዷል።

ባለ ብዙ ተሰጥኦው ዴቪድ ከተዋናይነቱ በተጨማሪ ተወዛዋዥ፣ ታሪክ ነጋሪ፣ እንዲሁም ባህል አዋቂ ከመሆኑም በላይ በዓለም ላይ የቀደምት ሕዝቦችን ውክልና በማጉላት ባበረከተው አስተዋፅኦ ዝናን አትርፏል።

ከአቦርጂን ዮልንጁ ከሚባለው ኩሩ ማኅበረሰብ የወጣው ዴቪድ በምዕራቡ ዓለምና በዮልንጁ ባህል መመላለስ ምን ይመስል እንደነበር በአንድ ወቅት አጋርቷል።

"በግራ ጎኔ አገሬ፣ በቀኝ ጎኔ ደግሞ በነጮች ዓለም ውስጥ ነኝ። በአንደኛው ጫፍ በካቪያርና በሻምፓኝ በተንቆጠቆጠ ቅንጡ ዓለም ውስጥ በሌላኛው በባህሌና በማንነቴ ውስጥ ነኝ" ብሎ ነበር።

በቀድሞው አጠራር አርነም ላንድ በአሁኒቷ አውስትራሊያ አህጉር ሰሜናዊ ግዛት ማርውዩ በሚባል ስፍራ ነው የተወለደው ዴቪድ። ዴቪድ የመጣበት ማኅበረሰብ (ጎሳ) ማንዳልፑይንጉ ይባላል።

ዴቪድ በዮልንጁ ባህልና ዕውቀት ሥርዓት ያደገ ሲሆን ይህም ሁሉም ፍጥረት የተሳሰረ እንደሆነ እንዲረዳ አድርጎታል። ዴቪድ የተዋጣለት አዳኝ፣ አቅጣጫ አዋቂ፣ ሙዚቀኛ፣ ሰዓሊ፣ የባህል ዳንስ አዋቂ እንዲሁም የማኅበረሰቡን መዋቅራዊ ሕጎች ጠባቂና ባላደራም ተብሎ የተሰየመ ነበር።

እናቱ እና አባቱ ካረፉ በኋላ ወደ ማኒንግሪዳ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተላከ። በዚህ ወቅትም ነበር ድንቅ የዳንስ ችሎታው በእንግሊዛዊው የፊልም ዳይሬክተር ኒኮላስ ሮግ ዕይታ ውስጥ የገባው።

ታዳጊውም በአውሮፓውያኑ 1971 ለተሰራው 'ዋክ አባውት' ለተሰኘው ፊልምና በጥቁር አገር ስለጠፉ ሁለት ነጭ ልጆች የሚነግር ታሪክ መሪ ገፀ ባህርይ እንዲጫወት ተመረጠ።

በዚህም ፊልም ላይ ዴቪድ እነዚህን ልጆች ለማዳን አንድ ከአቦርጂን ማኅበረሰብ የመጣ ግለሰብ የሚጫወተውን ሚናም ይተርካል።

በአውስትራሊያ የፊልም ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከአቦርጂን ማኅበረሰብ የተወለደ ግለሰብ ገፀ ባህርይ እንደ ጨዋ፣ ግርማ ሞገስ ያለውና ማራኪ ሰው ተደርጎ ሲሳል የዴቪድ ገፀ ባሕርይ የመጀመሪያው ነው። ሆኖም በፊልሙ መጨረሻ ላይ ስሙ በተሳሳተ መልኩ ነበር የተጠቀሰው።

ፊልሙ በአውስትራሊያ የፊልም ሰንጠረዥ ከፍተኛ ቦታን ማግኘት ቻለ። ከዚህም በላይ የዴቪድ ለየት ያለ የፊልም ተሰጥኦ፣ ግርማ ሞገስ፣ ውበት እንዲሁም ወንድነት ዓለም አቀፍ ርዕስ ለመሆን የበቃ ሲሆን ይህ ፊልም ከታላላቆቹ አንዱ የሚል ስፍራን ለማግኘት ችሏል።

ዴቪድ ጉልፒሊል ከተዋናዩ ሪቻርድ ቻምበርሌይን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወደ ካንስ ፊልም ፌስቲቫል ፊልሙን ለማስተዋወቅ በሚሄድበት ወቅት ለንደን በነበረው ቆይታ ከታዋቂው ሙዚቀኛ ጆን ሌነን ጋር በመዝናናት፣ ከጂሚ ሄንድሪክስ ጋር በመድረክ ላይ ሙዚቃ በመጫወት፣ ዕፀ ፋርስ (ማሪዋናን) ለመጀመሪያ ጊዜ ከቦብ ማርሌይ ጋር መሞከሩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።

እንዲሁም ስመ ጥር ከሚባሉት ከተዋናይ ማርሎን ብራንዶ፣ ከቦክሰኛው ሞሐመድ አሊ፣ ከተዋናዩ ብሩስ ሊ እና ከብሪታኒያንዋ ንግሥት ጋር በመገናኘቱ ስሙ እየናኘ ሄደ።

ዴቪድ በፊልም ዓለም ላይ ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ ቆይቷል። በአውስትራሊያ ሲኒማ ታሪክ ውስጥም ከፍተኛ ስፍራን ያገኙና በርካታ ሽልማትን መሰብሰብ የቻሉ ስኬታማ ፊልሞችን ሰርቷል።

ከነዚህም ታዋቂ ፊልሞች ውስጥ 'ስቶርም ቦይ'፣ 'ማድ ዶግ ሞርጋን'፣ 'ዘ ላስት ዌቭ'፣ 'ክሮኮዳይል ዳንዲ'፣ 'ዘ ትራከር'፣ 'ራቢት ፕሩፍ ፌንስ'፣ 'ዘ ፕሮፖዚሽን'፣ 'ቴን ካኖስ'፣ 'አውስትራሊያን' እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2014 የሰራው 'ቻርሊስ ካንትሪ' ይጠቀሳሉ።

ዴቪድ የተንቀሳቃሽ ምስል ባለ ብዙ ገፅታ ለማዝናናት እና ለማስተማር ያለውን ኃይል ከዮልንጁ ባህላዊ ሥርዓት ጋር ያመሳስለዋል። ቡንጉል ተብሎ የሚጠራው ባህላዊ ሥርዓት ቋንቋ፣ ድምፅና ትወናን በመጠቀም የዮልንጁን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ መንፈሳዊ ዓለማትን ውስብስብ ታሪኮች የሚገለጥበት መንገድ ነው።

የዮልንጁ የአኗኗር ዘይቤን የሚተርክና ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የሺዎች ዓመታት ታሪክ በርካቶችን በሚስብ መልኩም ወደ ሲኒማው ማምጣት ችሏል።

በአቦርጂን ማኅበረሰብ ላይ ያለውን አሉታዊ ትርክቶች ወደ ጎን በማለት እንዲሁም ከጥቁርነቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጨለምተኛ አስተሳሰቦችን በመግፋት፣ ከፊልም ሰሪዎች ጋር በመተባበር ያሳየው ፅናት የአውስትራሊያ ፊልም እና ቴሌቪዥን ከቅኝ ግዛት እሳቤ እንዲላቀቅ መንገድ ከፍቷል ተብሎም ይወደሳል።

ዴቪድ በትልቅ ስክሪን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመታየቱ በፊት ፊልም ሰሪዎች የአቦርጂን ማኅበረሰብ ገፀ ባህርያትን እንዲወክሉ እስያውያንን ወይም ነጭ ወንዶችን ጥቁር ቀለም ቀብተው ያሰሩ ነበር።

በርካታ ውጣ ውረዶችን በፅናት ያሳለፈው ተዋናዩ ከሦስት አስርት ዓመታት የፊልም ቆይታው በኋላ የአቦርጂን ማኅበረሰብን መወከል ብቻ ሳይሆን የዮልንጁ ታሪክ የሚተርከውን 'ቴን ካኖስ' የተሰኘውን ፊልም እንዲያዘጋጅ ታዋቂውን ፊልም ሰሪ ሮልፍ ደ ሄርን ማሳመን ቻለ።

ዝቅተኛ በጀት ያለው ባለብዙ ሽልማት አሸናፊው ይህ ፊልም ሙሉ በሙሉ በአቦርጂን ወይም በቶረስ ስትሬት ደሴት ቋንቋ የተቀረፀ የመጀመሪያው ፊልም ነው።

ዴቪድ በሚተርክበት በዚህ ፊልም "ጥሩ ታሪክ ነው፤ ሆኖም ከልብ ልታዳምጡት ይገባል። ምናልባት እናንተ እንደ ፊልሙ ታዳጊ ገፀ ባህርይ ዳይንዲ ልትሆኑ ትችላላችሁ። ምናልባትም የፊልሙ ታሪክ ህይወትን በምን መንገድ እንዴት በትክክል መኖር እንዳለባችሁ ያስተምራችኋል" ብሏል።

ዴቪድ ጉልፒሊል በትራከር ፊልም ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምንም እንኳን በፊልሙ ዓለም ዝናው ቢናኝም ከውጣ ውረድ የተላቀቀ አልነበረም። የራሱን የህይወት ታሪክ በሚዘክረው ጉልፕሊል በተሰኘውና በአውሮፓውያኑ 2004 አዴላይዴ አርትስ ፌስቲቫል ላይ በመድረክ የቀረበው ቲያትር ላይ በተባባሪ ፅሁፍ አዘጋጅነት ዕውቅና ቢያገኝም በፊልም በተቀየረው ፅሁፍ ላይ ግን እውቅና ተነፍጎት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2019 ነው በተባባሪ የፊልም ፅሁፍ አዘጋጅነት ዕውቅና የተቸረው። በመጨረሻም 'ማይ ኔም ኢዝ ጉልፒሊል' (የእኔ ስም ጉልፒሊል ነው') ለሚለውና የመጨረሻና መሰናበቻ ለሆነው ዘጋቢ ፊልሙም በተባባሪ አዘጋጅነት ስሙ ዕውቅና ተሰጠው።

የዴቪድ ውክልና እና እውቅና እየጨመረ በሄደ ቁጥር የምዕራባውያን ተፅዕኖም በትውልድ አገሩ እየተባባሰ መጣ። በአውሮፖውያኑ 2015 በሰራው 'አናዘር ካንትሪ' በተሰኘው ዘጋቢ ፊልሙ ከልጅነቱ በመጀመሪያ ወቅት ከነበረው ጊዜ ነጮች ወደ መኖሪያው አካባቢ ወደመጡበት የነበረውን ሁኔታ ይተርካል።

ሚስዮናዊያኑ በቀደምት ሕዝቦች መኖሪያ አካባቢ መጥተው ለጎሳው ቤት እንደሚሰራ አሳዩ፣ የአውስትራሊያ መንግሥት በአካባቢው ትምህርት ቤት ገነባ፣ ሱቅም ከፈተ እንዲሁም በደርዘን የሚቆጠሩ የአካባቢውን ጎሳዎች በአንድ ቦታ እንዲታጨቁ አደረገ።

የቀደምት ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ፖሊሲን በመንጠቅ 'በሰሜን ቴሪቶሪ' ጣልቃ ገብነት ተተካ። በአውስትራሊያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳፋሪ የሆነው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ደረሰባቸው።

ጣልቃ ገብነቱ ጥሩ ደመወዝ የሚከፈላቸው ነጮች ቤቶቹ ሲገነቡ ለዮልንጁ ማኅበረሰብ ደግሞ ገንዘባቸውን እንዴት እንደሚያወጡ የሚቆጣጠር መሰረታዊ ካርድ ተዋወቀ።

ገንዘባቸውን የሚቆጣጠረው ጀልባ ድንገት በአየር ጠባይ ምክንያት ድንገት ከዘገዬ ያለ ተፈጥሯዊ ምግብ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ብርሃን ሳያገኙ የሚቀሩባቸው ቀናት አሉ።

ከጊዜያትም በኋላ መብራት በአካባቢው ጠፋ፣ ነገር ግን ሆን ተብሎ የፈለጉትን ያህል ለስላሳ መጠጥና ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ ይቀርብላቸው ጀመር።

ዴቪድ ሲተርክም "መንግሥት አልኮልን ከመከልከሉ በፊት የታሰረ ሰው አልነበረም። ነገር ግን መንግሥት 25 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ ፖሊስ ጣቢያና የሕግ ማዕከል ገነባ። በቅርቡ መላው የከተማው ነዋሪ እስር ቤት መግባቱ አይቀርም" በማለት የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ በንዴት ሲስቅ ይሰማል።

የዴቪድ ጉልፒሊል ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2019 ዴቪድ ጉልፒሊል ሪድጂሚራሪል ዳላይትንግጉ የአውስትራሊያን የናይዶክ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማትን ተጎናጸፈ።

የሚማርክ ፈገግታ ያለው ባለራዕዩ ተዋናይ የብዙዎችን ልብ በመክፈት በርካቶችን የጥንታዊና ቀደምት ሕዝቦችን ታሪክ ማስተዋወቅ የቻለ ነው።

ከሁሉም በላይ የሚያውቁት ለጋስ፣ አስተዋይ፣ ባለ ግርማ ሞገስና የተከበረ የዮልንጁ ማኅበረሰብ ሽማግሌ እንደነበር ያስታውሱታል።

እሱ ቢያልፍም ትሩፋቱ በሰራቸው ሥራዎች ይቀጥላል።