በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚ ታንዛኒያዊ በአገራቸው ለምን ብዙም አልታወቁም?

የዛንዚባር ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዛንዚባር ተወላጁ አብዱልራዛቅ ጉርናህ የዘንድሮውን የሥነ ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት ሲያሸንፉ በዓለም ላይ በጣም የተወራላቸው ፀሐፊ ሆነዋል። ነገር ግን በአፍሪካ ቀርቶ በትውልድ አገራቸው ታንዛኒያ ብዙም አይታወቁም።

የ72 ዓመቱ ደራሲ ለአፍሪካውያን ጽሑፎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ተብለው አድናቆት አግኝተዋል፣ ተወድሰዋል፤ ነገርግን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሚገኙ የመጽሐፍት መደብሮች ውስጥ የአብዱልራዛቅ ድርሰቶችን ማግኘት ከባድ ነው።

አብዱልራዛቅ ባደጉበት እና በኋላም ከታንዛኒያ ጋር የተዋሃደችው የዛንዚባር ደሴት ላይ "የእሱን ፎቶ ብታሳዩ በርካቶች የሚያውቁት ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት ፎቶ ነው" በማለት በዛንዚባር መቀመጫውን ያደረገው ደራሲ እና ገጣሚ አሊ ሳሌህ ተናግሯል።

"በታንዛኒያ ውስጥ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ስለ ሥራው የሚያውቁት" በማለት አሊ የኖቤል ተሸላሚው ደራሲ ለአገራቸው እንዴት ባዳ እንደሆኑ ያስረዳል።

የአብዱልራዛቅ መጽሐፎች በዋነኝነት ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በኖሩባት እንግሊዝ ውስጥ ገበያ ላይ ይገኛሉ። ሆኖም 10 ልብወለዶቻቸው የሚያጠነጥኑት የትውልድ ቦታቸውና ለልባቸው ቅርብ በሆነችው ዛንዚባር ላይ ነው።

ቅኝ ግዛት በምሥራቅ አፍሪካ ማንነት ላይ ያለውን ተፅእኖ እንዲሁም ስደተኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ቀያቸውን ለቀው በሌሎች አገራት ሲኖሩ የሚፈጠረውን የመነቀልና ግራ የመጋባት ስሜትም በድርሰቶቻቸው ይዳስሳሉ።

ለስደትም ከእሳቸው በላይ ቅርብ የለም የዛንዚባር የአረብ ገዢ ልሂቃንን ከሥልጣን የገረሰሰው የአውሮፓውያኑ 1964 አብዮት ተከትሎ የተፈጠረውን ሁከት እና ብጥብጥ በመሸሽ ደራሲው በ18 ዓመታቸው ነው ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱት።

ከዚያ በኋላም የዛንዚባር ደሴት ከትልቋ ታንጋኒካ ጋር በመቀላቀል ታንዛኒያ ተመሰረተች። ደራሲው ለአስርት ዓመታት ያህል ሊነጥፍ ያልቻለ ከደሴቲቱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን ለብዙ ድርሰቶቻቸውም ዳራ ሆኗቸዋል።

"ለታንዛኒያውያን የአብዱልራዛቅን ድርሰቶች ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው። ድርሰቶቹም በአገር ውስጥ ሆኖ ታንዛኒያዊ ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም በባሕር ማዶስ? የሚሉ የማንነት ጥያቄዎችን በጥልቅ ይዳስሳል" በማለት ማኩኪ ና ዮታ የተባለው የታንዛኒያ አሳታሚ ዳይሬክተር ማኩኪ ብጎያ ይናገራሉ።

"ብዙውን ጊዜ ምሥራቅ አፍሪካውያን እንደመሆናችን መጠን ዓለምን የምናየው በሌሎች ሰዎች አይን ነው። ነገር ግን በአብዱልራዛቅ ሥራዎች ራሳችንንም ማየት እንችላለን" ይላሉ።

የመምህራን ሽሽት

የአብዱልራዛቅ የኖቤል ሽልማት ማሸነፍ በጥቅምት ወር ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ያለ ስመ ጥር ደራሲ ለአገሩ እንዴት ባዳ ሆነ የሚል ጥያቄም አጭሯል።

በተጨማሪም የአገሪቱ የንባብ ባህል እያሽቆለቆለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘም ክርክሮችን አስነስቷል።

የቲፒኤች መፃህፍት መደብር በዳሬሰላም

የፎቶው ባለመብት, Mkuki Bgoya

የምስሉ መግለጫ, የቲፒኤች መፃህፍት መደብር በዳሬሰላም

ከዛንዚባር አመፅ በኋላ አዲሱ አገዛዝ ለሥነ ጸሑፍ ብዙም ትኩረት ባለመስጠት ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ማሻሻያ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት በዛንዚባር የሚገኙት ሦስቱ ዩኒቨርስቲዎች አንዳቸውም የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ዘርፍን በዲግሪ ደረጃ አያስተምሩም።

"አብዮቱን ተከትሎ መንግሥት በርካታ የመጽሐፍት ክለቦችን እና ቤተ መጽሐፍትን ዘጋ። በርካታ ምርጥ የሚባሉ መምህራንም አገሪቱን ለቀው ወጡ" በማለት የዛንዚባር ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኢስማኤል ጁሳ ይናገራሉ።

"ለትምህርት የነበረው አተያይ ተቀየረ፤ የመማር ማስተማር ደረጃውም ወደቀ በዚህም የንባብ ባህሉም ተንኮታኮተ" ይላሉ።

በደሴቲቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በታንዛኒያም በተመሳሳይ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።

ባለፉት ዓመታት የታንዛኒያ ቤተ መጽሐፍት፣ ትምህርት ቤቶች እና የመጽሐፍት መደብሮች በመማሪያ መጽሐፍት እና ለትምህርት አጋዥ በሆኑ መጽሐፍት ላይ ያተኮሩ ሲሆን ይህም የልብ ወለድ ተደራሽነትን ገድቦታል።

ለበርካታ ዓመታት ልብ ወለድ ያልሆኑ እና ጋዜጦች ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑ የንባብ ዓይነቶች ሆነው ቢቆዩም፣ በመላው ዓለም የሚታየው የቴክኖሎጂ እድገት ወጣቱን በዲጂታል ሚዲያ ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል።

በዚህም ምክንያት የታንዛኒያ የህትመት ኢንዱስትሪ ሥነ ጽሑፎችን ለመሸጥ መንገታገት ጀምሯል።

እንደ ቅንጦት የሚታዩት መጽሐፍት

በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬ ሰላም የሚገኘው የማኩኪ ና ዮታ እህት ኩባንያ የሆነው ቲፒኤች የአብዱልራዛቅን ድርሰቶች ከሚሸጡ በጣም ጥቂት የመጽሐፍት መደብሮች አንዱ ነው።

"በታንዛኒያ ውስጥ በትምህርታዊ መጽሐፍት ላይ ብቻ በሚያተኩረው የሕትመት ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ክፍተት አይተናል። ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ልብ ወለድ፣ ግጥም እና ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ማሳተም እና መሸጥ ጀመርን። ዋናው ትኩረታችንም በተለይም በታንዛኒያውያን የተጻፉ ሥራዎች ላይ ነው" በማለት ብጎያ ያስረዳሉ።

"የአብዱልራዛቅ ልብወለዶች ለመሸጥ ረጅም ጊዜ በመውሰዳቸው እንደገና አላመጣንም" ይላሉ።

መኩኪ ብጎያና አብዱልራዛክ ጉርናህ

የፎቶው ባለመብት, Mkuki Bgoya

መጽሐፉ በርካታ ፈላጊ ከሌለው ዋጋውን ከፍ ያደርገዋል ይህም ሁኔታ ለበርካቶች የማይቀመስ ያደርገዋል።

"ገበያው ትንሽ ነው እናም በርካታ መጽሐፍት መቅረብ አይችሉም" ይላሉ ብጎያ።

"መጽሐፍት በጣም ውድ ናቸው፣ እናም በጥሬ ገንዘብ ተኮር ኢኮኖሚ ውስጥ የዋጋቸው ሁኔታ የቅንጦት ዕቃ ያደርጋቸዋል" በማለት ያስረዳሉ።

ምንም እንኳን ሌሎች በስዋሂሊ ቋንቋ የሚጽፉም ሆነ አፍሪካውያን ፀሐፍት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ቢካተቱም የአብዱልራዛቅ ድርሰቶች ግን የሉበትም።

"ከዛንዚባር ውጪ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ችሏል። ከአውሮፓያኑ 1967 ጀምሮ በአገር ውስጥ አልነበረም" ይላሉ ጁሳ።

"ከዚህም ጋር በተያያዘ አብዱልራዛቅ የሚታወቀው የዛንዚባር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን በሚከታተሉ ጥቂት አንባቢዎች ክበብ ብቻ ነበር።"

የስዋሂሊ ትርጉም በቅርቡ

አብዛኞቹ ታንዛኒያውያን የሚናገሩት እንዲሁም የኖቤል ተሸላሚው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ስዋሂሊ ቢሆንም አብዱልራዛቅ የሚጽፉት ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው።

የደራሲውን ሥራዎችም ወደ ስዋሂሊ ለመተርጎም እንደ አዲስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በለንደን የምሥራቃዊ እና አፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት የስዋሂሊ መምህር የሆኑት ዶ/ር አይዳ ሃድጂቫያኒስ ደራሲው አብዱልራዛቅ የኖቤል ሽልማት ከማግኘታቸው በፊት ድርሰቶቻቸውን ወደ ስዋሂሊ ቋንቋ መተርጎም ጀምረዋል።

መምህርቲቷ በአሁኑ ወቅት በሚቀጥለው ዓመት ሊወጣ ዕቅድ የተያዘለትን 'ፓራዳይዝ' የተሰኘ ሥራቸውን ትርጉም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ።

በአውሮፓውያኑ 1994 የታተመው 'ፓራዳይዝ' በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በታንዛኒያ ውስጥ ያደገ የአንድ ታዳጊ ታሪክ ነው።

ለበርካታ ታዋቂ ሽልማቶች የታጨው ይህ ድርሰታቸው በስዋሂሊ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ ሲበቃም አዳዲስ አንባቢዎችን ሥራውን እንዲያውቁት ያደርጋል ይላሉ።

"ታሪካችን፣ እውነታችንን እና ትዝታዎቻችንን በሚደንቅ መልኩ ድርሰቶቹ ላይ አሉ" በማለት የዛንዚባር ተወላጅ የሆኑት መምህርቷ ያስረዳሉ።

"ሥራው በምሥራቅ አፍሪካ ቢነበብ ተጽእኖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

የአብዱልራዛቅ ዝና በሥነ ጽሑፍ ዓለም በናኘበት በአሁኑ ወቅት ድርሰቶቻቸው የምሥራቅ አፍሪካ ባህል አንዱ አካል ሆነው የሚዘከሩበት ወቅት እንደሆነም ብዙዎች ይናገራሉ።

አንደ ቲፒኤች ያሉ በመላ አገሪቱ ያሉ የመጽሐፍት መደብሮች የአብዱልራዛቅ መጻሕፍትን ለማስመጣት እንደ አዲስ አዘዋል፤ በርካታ ጥያቄዎችንም እያስተናገዱ ነው።

ነገር ግን ይህም ቢሆን በቂ አይደለም በርካታ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ።

"አሳታሚዎች የራሳችንን የኖቤል ተሸላሚ በማስተዋወቅ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል መንግሥትም ይህን ማድረግ አለበት" ብለዋል ዶክተር አይዳ።

"የማንበብ ባህላችንን በአንድ ጀምበር መቀየር አንችልም፤ ስለዚህ የእርሱ ጽሑፎች እንዲነበብ የመጀመሪያ እርምጃዎች ፓራዳይዝ እና አፍተር ላይቭስ የተሰኙ ሥራዎቹን በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ማካተት ነው፤ የቀረው ይከተላል" ብለዋል።