ዩኬ በ11 የአፍሪካ አገራት ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ ዕቀባ አነሳች

በሂትሮው ማረፊያ ያለ ተጓዥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩኬ መንግሥት ከአዲሱ ኦሚክሮን የኮቪድ ተህዋሲ ዝርያ ጋር በተያያዘ በ11 የአፍሪካ አገራት ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ ዕቀባ ማንሳቷን አስታወቀች፡፡

አገራቱም አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ናቸው፡፡

እነዚህ አገራት በዩኬ የጎዞ ዕቀባ የተጣለባቸው ባለፈው ኅዳር ወር የኦሚክሮን ተህዋሲ ዝርያ ከዚሁ ደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ መገኘቱን ተከትሎ ነበር፡፡

የዩኬ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሳጂድ ጃቪድ እንዳሉት ዕቀባውን ማንሳት ያስፈለገው ተህዋሲው አሁን በስፋት በሌሎች ቦታዎችም መሰራጨቱ ስለተረጋገጠ በነዚህ አገራት ላይ ጫና አድርጎ መቆየቱ ትርጉም ስለሌለው ነው፡፡

ሚኒስትሩ ለዩኬ ፓርላማ እንዳብራሩት፣ የኮቪድ ተህዋሲ አዲሱ ዝርያ ኦሚክሮን በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሳይቀር ገብቶ እያለ፣ እንዲሁም በሌሎች በርካታ የአውሮጳ አገራት መዛመቱ እየታወቀ እነዚህን ዐሥራ አንድ የአፍሪቃ አገራት በዕቀባ ዝርዝር ማቆየት ትርጉም አልባ ነው፡፡

ለወረርሽኝ ተጋላጭ አደገኛ አካባቢ በሚል ከተዘረዘሩ አገራት ወደ ዩኬ የሚገቡ ተጓዦች ለ10 ቀናት ራሳቸውን ለይተው መንግሥት ባዘጋጃቸው ሆቴሎች መቆየት ይኖባቸዋል፡፡

ወጪውን የሚችሉትም ተጓዦቹ ይሆናሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በርካታ ተጓዦች ለሆቴል ቆይታ ብዙ ገንዘብ ወጪ እንዲያደርጉ መገደዳቸው ቅሬታ ፈጥሮባቸው እንደነበር ሲዘገብ ነበር፡፡

በዩኬ ከአዲሱ የኦሚክሮን የኮቪድ ዝርያ ጋር በተያያዘ አንድ ሰው መሞቱ የተዘገበው ትናንት ነበር፡፡