የመንደር ውል ሕጋዊ ነው? በመንደር ውል ቤት ስንሻሻጥ ልብ ልንላቸው የሚገቡን ቁልፍ ነጥቦች

በእስክቢርቶ ወረቀት ላይ የሚፈርም እጅ

የፎቶው ባለመብት, Pheelings Media

የአገሪቱ አዋዋይ በተለምዶ 'ውልና ማስረጃ' የምንለው መሥሪያ ቤት ነው።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ደግሞ ሙሉ ስሙ ነው። አሁን ግን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።

ነገሩ ከወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም።

ከሐምሌ ወዲህ ይኸው እስከዛሬም አገልግሎት እየሰጠ ያለው በከፊል ነው። የተንቀሳቃሽ ንብረት ሽያጭን ጨርሶውኑ እያዋዋለ አይደለም።

ይህን ተከትሎ ዜጎች በስፋት በመንደር ውል ተጠምደዋል። "ላልከዳህ-ላልክድህ ቃል አለኝ" እያሉ በየመንደሩ እየተፈጣጠሙ ነው።

ለመሆኑ በውልና ማስረጃ ያልተረጋገጡ የመንደር ውሎች በሕግ ፊት ተቀባይነት አላቸው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ ሁለት ከፍተኛ የሕግ አማካሪና ጠበቆችን አነጋግሯል።

ጠበቃ ሚካኤል ተሾመ እና ጠበቃ ታምራት ኪዳነማርያም ይባላሉ። ሕጉን እያመሳከሩ፣ በሥራ ተሞክሮ የሚገጥሟቸውን እያጣቀሱ ጉዳዩን በየፈርጁ ይተነትኑልናል።

ውል የሚጸናው ምን ሲሟላ ነው?

አራት ነገር ካልተሟላ ውል አይጸናም ይላሉ ጠበቃ ሚካኤል።

1ኛ• ፈቃድ (Consent) ነው። ተዋዋዩ ፈቃዱን የሰጠው ወዶና ፈቅዶ በማያሻማ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል። ምን ማለት ነው ይሄ፣ በመታለል/በማታለል የተፈጸመ ውል ዋጋ አይሰጠውም።

2ኛ• ተዋዋዮቹ በሕግ 'ችሎታ ያላቸው' መሆን አለባቸው። 'ችሎታ' የሕግ ትርጉሙ ሁለት ነው። የተዋዋዮች ዕድሜ ከ18 ዓመት በላይ መሆን እና የአእምሮ ጤና ነው።

3ኛ• የውሉ ዋና ጉዳይ በሕግ የሚፈጸም መሆን አለበት። ለምሳሌ ባዶ መሬት መሸጥ አይቻልም። ስለዚህ የባዶ መሬት ሽያጭ ውል ቢደረግም በፍርድ ቤት ውድቅ ነው። ሌላስ?

4ኛ• የውል አቀራረጽ ወይም ፎርም ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ለማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሸጥ 2 ምስክሮች መኖራቸው፣ በውል አዋዋይ ፊት መረጋገጥ፣ ሕጉ ያስቀመጣቸው ዝርዝሮች መሟላት ማለት ነው።

የሆነስ ሆኖ፣ የመንደር ውል ሕጋዊ ነው?

ጠበቃ ሚካኤል፣ ለዚህ ጥያቄ በአጭሩ "ሕጋዊ አይደለም" የሚል መልስ ይሰጣሉ።

ጠበቃ ታምራት ደግሞ "ነውም፣ አይደለምም" የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። ይህን ያሉበትን ምክንያት ወደ ኋላ ላይ ያስረዱናል።

አሁን ወደ ጠበቃ ሚካኤል ነጥቦች እንመለስ።

ጠበቃ ሚካኤል ለዚህ ድምዳሜ ያበቃቸውን ነጥብ ሲያስረዱ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፣ ማለትም ቤትና መሬት በርካታ ሰዎች በመንደር ውል የሚሻሻጡ ቢሆንም በርካታ ሰዎች ተግባሩን ስላደረጉት ግን ሕጋዊ አያሰኘውም ይላሉ።

ይህ የመንደር ውል በሕግ ተቀባይነት የማይኖረው የሰነድ ማረጋገጥ ዋና ዓላማን የሚጥስ መሆኑ ነው ይላሉ።

ሰነድ ለምን ይረጋገጣል? ባይረጋገጥስ ምን ችግር አለው? ከሚለው እንጀምር።

ጠበቃ ሚካኤል 'ሰነድ ለሁለት ዓላማ ነው የሚረጋገጠው' ብለው የክርክሩን ፍሬ ነገር ያሲዙናል።

አንደኛ በተዋዋዮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመግዛት ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሦስተኛ ወገን ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው።

ሦስተኛ ወገን የሚባሉት እነማን ናቸው ያልን እንደሁ፣ ከገዥና ሻጭ ውጪ ያሉ የትኛውንም ወገኖችን ያካትታል።

ለምሳሌ የመንግሥት አካል፣ የክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር፣ ባንክ፣ ለምሳሌ ሽያጩ ይፍረስልኝ የምትል/የሚል ሚስት/ባል . . . ወዘተ እነዚህ ሁሉ 3ኛ ወገን ይባላሉ።

ከእነዚህ አካላት አንዱ፣ እንበልና በመንደር ውል በተፈጸመ ንብረት ላይ ጥያቄ ቢያነሱ ሙግቱን ያለምንም እሰጥ አገባ አሸነፉ ማለት ነው።

በመንደር ውል ቤት የገዛ ሰው ቀለጠ ማለት ነው።

በአጭሩ ውል የሚረጋገጥበት ዋንኛ ዓላማ ሦስተኛ ወገኖች ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው።

"የመንደር ውል ችግሩም ይሄ ነው" ይላሉ ጠበቃ ሚካኤል።

እርግጥ ውል በሰነዶች ሲረጋገጥ መንግሥት ቴምብር ያሳርፍበታል። ገቢ ያገኛል።

ገዥና ሻጭ ሰነዱን ይዘው ክፍለ ከተማ ሲሄዱ የመንግሥት አካል ቀረጥ ይጥላል። ከዚያም ገቢ ይገኛል።

ተዋዋዮች ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ስለቀረቡ፣ ሕጋዊ አገልግሎት አግኝተው የስም ማዞርያ አሹራ ይከፍላሉ። ይህም ሌላ ገቢ ነው።

ለዚህም ነው ውሉ በሕጉ ላይ የተቀመጠውን ፎርም ስላሟላ እንደ ሕጋዊ ውል ተቆጥሮ ተፈጻሚነት የሚኖረው ይላሉ ጠበቃ ሚካኤል።

ተፈጻሚነት ይኖረዋል ማለት ግን ምን ማለት ነው?

በአጭሩ ለምሳሌ ሻጭ ለገዢ ስም አላዞርልህም ቢል ፍርድ ቤት ከሶ በግዴታ ስም እንዲያዞር፣ ገዥ ላይ ለደረሰው ኪሳራም ካሳ እንዲያገኝ ይሆናል ማለት ነው።

ይህን ዕድል ግን በመንደር ውሎች ላይ ለማሳካት አስቸጋሪ ይሆናል።

በመንደር ውል የተሸጠ ንብረት እጣ ፈንታው ምንድነው?

በፍርድ ቤት ቀርቦ ያልተመዘገበ ውል፣ ወይም በውል አዋዋዮች ፊት ያልተረጋገጠ የመንደር ውል እንደ ሕጋዊ ተቆጥሮ አፈጻጸም ሊቀርብበት አይችልም።

በዚህ ላይ ምንም ብዥታ መኖር የለበትም ይላሉ ጠበቃ ሚካኤል።

ሆኖም ግን የመንደር ውሎች አሁንም በብዙ ሰዎች ዘንድ ይሠራባቸዋል። ውልና ማስረጃ አገልግሎት ስላቆመ ብቻ ሳይሆን ድሮም ይሠራባቸዋል።

የሚገርመው ፍርድ ቤትም በብዛት እነዚህን በመንደር ውል የተፈጣጠሙ አቤቱታዎች ይመለከታል። ለምን?

የመንደር ውል ሕጋዊ ካልሆነ ለምን ፍርድ ቤት ይመለከተዋል? ለምን "ወዲያልኝ! ሲጀመር፣ ይሄ ሕጋዊ ውል አይደለም" ብሎ አሽቀንጥሮ አይጥለውም?

ጠበቃ ሚካኤል "ሕግ በባህሪው አስተናጋጅ (Flexible) መሆን ስላለበት ነው" ይላሉ።

የፍርድ ቤት መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉዳዩን ሲያብራሩም፣ የመንደር ውል ተዋዋዮች፣ 'አዎ የመንደር ውል አድርገናል' ብለው ሳይካካዱ የሚያነሱት ጉዳይ ውሉ የመንደር ውል ነውና 'ፎርምን ብቻ አላሟላም' ተብሎ ውድቅ አይደረግም የሚል መረዳት በፍርድ ቤት አካባቢ ስላለ ነው ይላሉ።

ጠበቃ ታምራት በዚህ በአቶ ሚካኤል ነጥብ ይስማሙና ነገር ግን በመንደር ውል ሕጋዊነት ዙርያ ያለው ብዥታ "እኛ የሕግ ባለሞያዎችም እርግጠኛ ሆነን ምክር መስጠት እስክንቸገር የሚያደርሰን ሆኗል" ይላሉ፡፡

ነገሩን ሲያፍታቱት፣ በመርኅ ደረጃ አንድ ውል በመንደርም ይደረግ በውል አዋዋይ ፊትም ይደረግ፣ በቃልም ይደረግ ሕጋዊ መሆኑን በማስመር ይጀምራሉ።

ሆኖም ሕግ የግድ በጽሑፍ መሆን አለባቸው የሚላቸው የውል ዓይነቶች አሉ። ከእነዚህ አንዱ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ነው።

የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በጽሑፍ መሆን አለበት፣ በሁለት ምስክሮች ፊት መሆን አለበት። በአዋዋይ ፊት መሆን አለበት።

አሁንም ጥያቄውን እንድገመው። ውሉ በመንደር ቢደረግ እጣ ፈንታው ምንድነው የሚሆነው?

ጠበቃ ታምራት "እውነት ለመናገር በዚህ ረገድ ሕጉ የተረጋጋ አይደለም" ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ላይ ቁርጥ፣ ጥርት ያለ መልስ እስከዛሬ ፍርድ ቤቶች አልሰጡም።

የአገሪቱ የመጨረሻ ፍርድ ቤት የሆነው ሰበርም ቢሆን ከውል አዋዋይ (ውልና ማስረጃ) ውጪ የተደረጉ የመንደር ውሎች ይፀናሉ ወይስ አይፀኑም በሚለው ላይ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ውሳኔ መስጠቱን ያወሳሉ።

በአንድ በኩል፣ ሰዎች በመንደር ከተዋዋሉና ነገር ግን ፊርማቸውን ካልተካካዱ ውሉ በተዋዋዮቹ መካከል ብቻ ይጸናል ብሎ የወሰነበት ፍርድ አለ።

ይህ ማለት ውሉ የሚጸናው በእነሱ ላይ ብቻ ነው። ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ላይ መቃወሚያ ሆኖ ሊቀርብ ግን አይችልም።

ምን ማለት ነው፣ አንድ ሰው ቤቱን በመንደር ውል ቢሸጥና ውል ለማፍረስ ፍርድ ቤት ቢሄድ ገዥ ገንዘቡን ለመክፈል ይገደዳል። ሻጭም ቤቱን ለመስጠት ይገደዳል።

ሆኖም ግን፣ ለምሳሌ ባንክ በቤቱ ላይ ጥያቄ ቢኖረው የመንደር ውሉ አይጸናበትም።

ወይም ደግሞ ሻጭ ላይ ባለ ዕዳ የሆነ ሰው ዕዳዬ ቤቱ ተሸጦ ይከፈለኝ ቢል ቤቱ ተሸጧልና አይከፈልህም ሊባል አይችልም። ምክንያቱም በመንደር ውል ስለተሸጠ።

አደጋውም እዚህ ላይ ነው።

ገዢው የመንደር ውሉን ይዞ "እኔ እኮ ይሄን ቤት ገዝቼዋለሁ" ብሎ ጥያቄ ያነሱ ሦስተኛ ወገኖችን ዝም ሊያሰኛቸው አይችልም።

ስለዚህ ገዢ በመንደር ውል መፈጣጠሙ "ወዶና ፈቅዶ በራሱ ላይ አደገኛ አደጋን ጋብዟል" ይላሉ ጠበቃ ታምራትና ጠበቃ ሚካኤል።

ተዋዋዮች የመንደር ውልን ለምን ተመራጭ ያደርጋሉ?

አሁን አሁን የተለመደው አሰራር ገዥና ሻጭ ውል የሚፈጽሙት በሁለት ዙር ነው።

መጀመሪያ በመንደር ውል ይፈጣጠሙና ነው ወደ ሁለተኛ ውል አዋዋይ ዘንድ የሚመጡት።

ብዙውን ጊዜ አንድ ቤት ስንት እንደተሸጠ በትክክል የሚታወቀውም በመንደር ውል ላይ እንጂ በትክክለኛው ውል ላይ አይደለም።

ተዋዋዮች ወደ መንግሥት ተቋማት ሄደው የሚዋውሉት በ2ኛ ደረጃ ነው። ይህን ሲያደርጉም ብዙውን ጊዜ ዋጋ ቀንሰው ነው።

"…ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው ትክክለኛ ዋጋ ተናግረው የሚዋዋሉት። መንግሥት ቢቸግረው ተመን አውጥቶ ያስክፍላል። 6 በመቶ አሹራ ትከፍላለህ። የተዋዋልከው ከተመኑ ከፍ ካለ በተዋዋልከው ያስከፍላል። ዝቅ ካለ ደግሞ በተመኑ ያስከፍላል" ይላሉ ጠበቃ ታምራት።

ጠበቃ ሚካኤል በበኩላቸው ይህ የሁለት ጊዜ ውል ብዙ ሰው ልብ ባይለውም አደጋ አለው ይላሉ። እንዴት?

በሁለት ዓይነት ዋጋ መፈራረም የሚያመጣው አደጋ ስምምነት ሲፈርስ ነው።

አንድ ሰው ለምሳሌ ውል ይፍረስልኝ ብሎ ፍርድ ቤት ሲሄድ ውል ይፈርሳል። ውል ሲፈርስ ደግሞ ወደነበረበት ነው የሚመለሰው። ሻጭ ገንዘብ ይመልሳል፣ ገዥ ንብረቱን ይመልሳል።

በአሥር ሚሊዮን ብር የተሸጠ ቤት ውልና ማስረጃ ባረጋገጠው ውል፣ ፍርድ ቤት ተሂዶ ውል ቢፈርስ ተዋዋዮቹ ዋጋ ዝቅ አድርገው ስለሚዋዋሉ [ለምሳሌ 6ሚሊዮን ብር] ሻጭ ገንዘብ መልስ ይባላል።

ይህን ጊዜ እንዲመልስ የሚገደደው በውልና ማስረጃ በገዛበትን ገንዘብ ነው።

ይህ ማለት ገዥ 4 ሚሊዮን ብር መክሰሩም አይደል?

ጠበቃ ታምራት በበኩላቸው ዜጎች የመንደር ውልን የሚመርጡት በዋናነት ቀላልና ምቹ ስለሆነ ነው ይላሉ።

ሕጋዊው አሠራሩ ጥብቅ ነው፤ በርካታ ሰነዶች መሟላትን ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው።

ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያነሱት ካርታን ነው።

"አይደለምና በገጠር፣ በአዲስ አበባ ስንቱ ቤት ነው የተሟላ ካርታ፣ የተሟላ ሰነድ ያለው? ስንቱ ከተማ ነው ማዘጋጃ ቤትስ ያለው?"

ካርታው ስሙ ባንተ ነው ወይ? ዕዳና ዕገዳ የለበትም ወይ? ይሄ ሁሉ ነገር ከክፍለ ከተማ መጣራት አለበት።

አቶ ታምራት "መጣራቱ በጎ ነው፣ ክፋት የለውም" ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን ሰዎች በተለያየ ምክንያት የሚጠየቁትን ሁሉ ለማሟላት ይቸገራሉ ይላሉ።

"አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ችግሩን እያወቁም ከነጉድለቱ ንብረቱን መግዛት ይፈልጋሉ። አትግዙ ልንላቸው ነው? ገዢ የፍርድ ቤት ዕግድ መኖሩን እያወቅኩ ልግዛ ቢልስ? ልንከለክለው ነው?"

ልብ የማንላቸው የመንደር ውል አደጋዎች

የመንደር ውል ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለውን ሙግት እረፍት እንስጠውና ወደ አንድ ቁልፍ ነጥብ እንሻገር።

የመንደር ውል ይዞብን የሚመጣው ፈተና ምንድነው? ሁለቱ ጠበቆች የነገሩንን በአጭር በአጭሩ እናካፍላችሁ።

አንድ የቤት ገዥ በመንደር ውል ከተዋዋለ በኋላ ያን ይዞ ክፍለ ከተማ ሄዶ ስም ይዙርልኝ ቢል ተቀባይነት የለውም።

አንድ ቤት ገዥ ቤቱን በመንደር ውል ገዝቶ አገር ሰላም ብሎ እየኖረ ድንገት የ3ኛ ወገን ጥያቄ ቤቱ ላይ ቢነሳ ለከፍተኛ ቀውስ ይጋለጣል።

ይህም ከሻጭ ባል/ሚስት የሚመጣ፣ "ውሉ ውድቅ ይደረግልኝ" የሚል ጥያቄ ሊሆን ይችላል።

በመንደር ውል ያገባ/ያላገባ ሰነዶች ጋር ተያይዞም ብዙ አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ።

ኋላ ላይ በሚመጣ መቃቃር ፍቺ ቢኖር ገዢ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል።

አንድ ቤት ገዥ አገር ሰላም ብሎ ቤት በመንደር ውል ገዝቶ እየኖረ፣ የሻጭ ባል/ሚስት ሽያጩ አይመለከተኝም ይፍረስልኝ ብትል/ቢል፣ ቤት ገዢ ከፍተኛ የፋይናንስና የሥነ ልቡና ጉዳት ይደርስበታል።

የመንደር ውሉን ይዞ ፍርድ ቤት ቢሄድም አትስተናገድም ባይባልም፣ ከሻጭ ገንዘቡን መልሶ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው የሚሆነው።

"እንዲህ ዓይነት በርካታ ጉዳዮች ያጋጥሙናል፣ ሽያጭ ውሉ አይመለከትኝ የሚሉ የትዳር አጋሮች ይኖራሉ። በቤተሰብ ሕጉ ከ500 ብር በላይ የሚደረግ ሽያጭ የሁለቱንም ይሁንታ ማግኘት አለበት፤ በዚህ የተነሳ የመንደር ውል ያልታሰበ ጣጣ ይዞ ይመጣል" ይላሉ አቶ ሚካኤል።

ለምሳሌ መንግሥት ይህን ክልከላ ሲያነሳ ሥራ በቆመበት ወቅት በመንደር ውል የተዋዋላችሁ በሙሉ ውላችሁ ውድቅ ነው ቢል በርካታ ሰዎች ገንዘብ መልስልኝ-አልመልስም አተካራ ውስጥ ሊከታቸው ይችላል።

ይህ ባይሆን እንኳ እነዚህ ሰዎች የመንደር ውላቸውን ለማጽደቅ ውልና ማስረጃ ሲሄዱ ገንዘብ በባንክ ያስተላለፋችሁበትን ሰነድ አምጡ ይባላሉ።

በዚህን ጊዜ ሻጭ የተቀበለው ገንዘብ ተመናምኖበት ይሆናል። ገዥ ያን ከፍተኛ ገንዘብ በድጋሚ በባንክ ለማስተላለፍ ይቸገር ይሆናል። እጁ ላይ አይኖረውም ይሆናል።

የቤት ዋጋ በየጊዜው ከመናሩ ጋር ተያይዞ ደግሞ ሻጭ በአዲሱ የዋጋ ተመን ሊማልልና ሐሳቡን ሊቀይር ይችላል።

የከፈልኩን ቀብድ መልስልኝ አልመልስም ጣጣ ሊከተል ይችላል።

በዚህ መካካድ መካከል የመንደር ውል ተይዞ ፍርድ ቤት ሲኬድ፣ ፍርድ ቤት ተዋዋዮቹ ውል ማድረጋቸውን እስካልተካካዱ ድረስ ያስተናግዳቸዋል።

ነገር ግን ሻጭ በውሉ የሚገደደው በመንደር ውሉ የተመላከተውን የገንዘብ መጠን ብቻ ነው።

በሐሰተኛ የብድር ውል የሚፈጸሙ የመንደር ውሎችም ዘርፈ ብዙ ጣጣን ያስከትላሉ።

የብር የመግዛት ዋጋ መውረድና የቤት ዋጋ መጨመር ሻጭ በጊዜ ሂደት ሽያጩን ክዶ፣ ገንዘብ እንዲመልስ የሚያማልል ነው።

"…ብቻ በአጠቃላይ በመንደር ውል ገዥው በራሱ ላይ የሚጋብዘው አደጋ የትየሌሌ ነው" ይላሉ ጠበቃ ሚካኤል።

አቶ ታምራት በበኩላቸው በመንደር ውል ስንዋዋል አንዳንድ ጊዜ ይሆናሉ ብለን የማንጠብቃቸው ነገሮችም እንደሚከሰቱ መዘንጋት የለብንም ሲሉ ያስገነዝባሉ።

"…ለምሳሌ በመሀል ሞት አለ። ከአገር መውጣት አለ። ውክልና ማንሳት አለ። በሰው ላይ ነገ ምን እንደሚደርስ ማን ያውቃል?"

አቶ ሚካኤል በበኩላቸው፣ "በመንደር ውል የተፈጣጠመ ሻጭ ቢሞት የውርስ ጉዳይ ይከተላል፣ ጋብቻ ቢፈርስ የቤተሰብ ክርክር ውስጥ ይገባል፣ ወራሾች ቤቱ በሕገ ወጥ ውል የተፈጸመ ነው ብለው ሊያሳግዱት ይችላሉ። ጣጣው ብዙ ነው።"

ጠበቃ ታምራት እንዲያውም ነገሩ ከዚህም የከፋ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ጠቅሰዋል።

"አንዳንድ መጥፎ ሰዎች ያጋጥማሉ። አንድን ቤት በመንደር ውል ለሁለት እና ለሦስት ሰው ከሸጡ በኋላ 'በሉ ሥራችሁ ያውጣችሁ' ብለው የሚሰወሩ።"

ታዲያ ምን ይሻላል?

ጠበቃ ሚካኤል፣ ምክራቸው አንድ ነው። "በቃ፣ የመንደር ውል ይቅርብን" የሚል።

የግድ ከሆነስ?

የግድ ከሆነም ውሉ መዘጋጀት ያለበት በሕግ አዋቂዎች ነው ይላሉ።

ምክንያቱም አሁን ያሉ ውሎች ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድና-ወጥ (standard) ናቸው። በጠበቃ ቢዘጋጁ ግን የሻጭና ገዢ ግዴታን በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣሉ። ከዚያም ባሻገር ነገ ሊመጣ የሚችልን የሕግ ክፍተትን መድፈን ይቻላል።

ጠበቃ ታምራት በበኩላቸው የውሎች ወጥ መሆን በራሱ ችግር አይደለም ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ወጥ ተደርገው የተበጁ ውሎች በየጊዜው ክፍተቶቻቸው እየተሞሉ መሄድ አለባቸው ባይ ናቸው።

ዞሮ ዞሮ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመንደር ውልን ጨርሶ ማቆም እንደማይቻል ያምናሉ።

ተዋዋዮች አውቀው እስከገቡበት ድረስ አታድርጉት ሊባሉም አይችሉም።

ሆኖም ውል ማዋዋል በውጭ አገር እንደሚደረገው በጠበቆች በኩል (ፕራይቬታይዝ) ቢደረግ የሚል አዲስ ሐሳብ አላቸው።

ይህ ሐሳብ ራሱን ችሎ መፍታታት የሚፈልግ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል።

አሁን ጥያቄው የመንደር ውል ይቅርብን ወይስ? የሚለው ነው።

አቶ ታምራት ሐሳባቸውን የሚጠቀልሉት በምሳሌ ነው።

"የመንደር ውልን እንደ ሕክምና እንውሰደው። እጃችንን ሳንታጠብ ብንበላ ልንታመመም እንችላለን፤ ላንታመም እንችላለን። ታጥበን ብንበላ ግን ጥሩ ነው።"