ሩምባ የተሰኘው የኮንጎዎቹ ሙዚቃና ዳንስ በዩኔስኮ ወካይ ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ

በሩምባ ሙዚቃ የሚታወቀው ፓፓ ዌምባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሩምባ ሙዚቃ የሚታወቀው ፓፓ ዌምባ

በአፍሪካ ሙዚቃ እና ውዝዋዜ ዘርፍ ከፍተኛ ስፍራ ያለው የኮንጎዎቹ ሩምባ በዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

ሙዚቃና ዳንስን ያጣመረው ሩምባ በዩኔስኮ በቅርስነት እንዲመዘገብ ዘመቻ ሲያካሂዱት የነበሩት ሁለቱ ኮንጎ ናቸው - ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክና ኮንጎ ብራዛቪል።

ሁለቱም በአንድ ወቅት ጥንታዊ የተባለችውን የኮንጎ ግዛትን ተቆጣጥረዋል። ሁለቱም አገራት ባቀረቡት መረጃ መሰረት ሩምባ ምንጩና መነሻው ከዚህች ጥንታዊ ግዛት ነው።

"ሩምባ" የሚለው ስርወ ቃሉም ኪኪኮንጎ ቃል "ንኩምባ" ሲሆን ትርጉሙም እምብርት ማለት ነው።

የኮንጐ ሩምባ እንደ የጃማይካ ሬጌ ሙዚቃ እና የሲንጋፖር የሃውከር ምግብ በዩኔስኮ "ወካይ የማይዳሰስ የሰው ልጅ ባሕላዊ ቅርስ" ዝርዝር ውስጥ ገብቷል።

የተባበሩት መንግስታት የባህል አካል፣ ዩኔስኮን ይህንን የቅርስነት ደረጃ መስጠት "በማደግ ላይ ባለው ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ውስጥ የባህል ብዝሃነትን ለመጠበቅ ይረዳል" ብሏል።

ሙዚቃው እና ውዝዋዜው በ20ኛው ክፍለ ዘመን የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ተምሳሌት ሆኗል ሲሉ የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሪ አዙላይ ገልፀው "በአሁኑ ጊዜ ሙዚቃው ያለው ፖለቲካዊ ባህርይ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አርቲስቶችን የሚያነሳሳ ነው" ብለዋል ።

ምንም እንኳን ሩምባ አፍሪካዊ መነሻ ያለው ቢሆንም፣ ከአህጉሪቱ ውጪ ባሉ በርካቶች አእምሮ ውስጥ ያለው ሩምባ ከላቲን ዳንስ ጋር ይበልጥ የተቆራኘ ነው።

በእርግጥ፣ የኩባ ሩምባ በአውሮፓውያኑ 2016 በዩኔስኮ የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ሆኖም ተመዝግቧል።

"ሩምባ የማንነታችን አካል፣ በየትኛውም አገራት ለሚኖሩ አፍሪካውያን ዝርያ ላላቸው ሁሉ የሁላችንም አካል ነበር" በማለት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የባህል ሚኒስትር ካትሪን ካትሁንጉ ፉራሃ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ተናግረዋል።

አክለውም "ሩምባ የእኛ ነው ተብሎ እንዲታወቅ እንፈልጋለን። ማንነታችን ነው።" ብለዋል።

"ወደ ውጭ አገር በባርነት የተጋዙ ቅድመ አያቶቻችን ታሪካቸውን፣ አመጣጣቸውን፣ ትዝታቸውን ለማስታወስ ሲፈልጉ የእምብርት ዳንስ ጨፍረዋል። ይህም ሩምባ ነው" በማለት ተናግረዋል።

ሩምባ የሚደንሱ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images