ኮቪድ-19፡ ኦሚክሮን በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ

ፈረንሳይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአውሮፓ የኮቪድ ልውጥ ዝርያ የሆነው ኦሚክሮን በብርሃን ፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነና በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ በፈረንሳይ ከሌሎቹ ዝርያዎች በላይ ሊሆን እንደሚችል የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂያን ካስቴክስ አስጠነቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አርብ ዕለት ፈረንሳይ ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለሚገቡ ተጓዦች ጥብቅ የጉዞ እገዳ ከመጣሏ ከሰዓታት በፊት ነው።

ዩኬ በቀጠናው ካሉ አገራት በአዲሱ ልውጥ ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተመታች አገር ሆናለች። አርብ ዕለት ብቻ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኦሚክሮን መያዛቸው ተረጋግጧል።

የአውሮፓ አህጉር የጤና ባለሥልጣናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ እየጣሩ ነው።

የጀርመን፣ የአየርላንድ ሪፐብሊክ እና የኔዘርላንድስ መንግሥታት ወረርሽኙን ለመግታት ተጨማሪ እገዳ መጣላቸውን አስታውቀዋል።

በጀርመን አርብ ዕለት ብቻ 50 ሺህ ሰዎች በኦሚክሮን መያዛቸውን ጤና ሚኒስትር ካርል ሉተርባች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የጤና ሚኒስትሩ "አገሪቷ ለሚገጥማት ፈተና በደንብ መዘጋጀት አለባት" ብለዋል።

በአየር ላንድም በልውጡ የኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ማይክል ማርቲን እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወረርሽኙ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ ይህን ያሉት ዩኬ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ከፍተኛውን በኮቪድ የተያዙ ሰዎችን መመዝገቧን ተከትሎ ነው። በሦስት ቀናት ውስጥ በአብዛኛው በልውጡ ቫይረስ የተያዙ ከ93 ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል።

በዚህም ምክንያት ፈረንሳይ ከዩኬ ለሚገቡ ጎብኝዎች እና የንግድ ሰዎች አርብ ዕለት ድንበሯን ዘግታለች። እገዳው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ወደ አገሪቷ ለመግባት የዶቨር እና ዩሮስታር ወደብ መግቢያዎች በሰዎች ተጨናንቀው ታይተዋል።

ሚኒስትር ካስቴክስ አዲሱ የጉዞ እገዳ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የተወሰደ ጥብቅ እርምጃ አካል ነው ብለዋል።

ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለወሰዱ ሰዎችም ሦስተኛ ዙር ክትባት ለመወሰድ መጠበቅ ያለባቸው ጊዜ እንዲያጥርም ተደርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ ምግብ ቤት ለመግባትና ረዥም ርቀት በሕዝብ መጓጓዣ ለመጓዝ ሙሉ ክትባቱን መውሰድ ይጠበቃል።

ከዚህም ባሻገር የአዲስ ዓመት የዋዜማ በዓል እና የርችት ትዕይንቶች ተሰርዘዋል።

ካስቴክስ አክለውም መንግሥት ክትባቱን ለመውሰድ እየታየ ያለውን ማመንታት ለመቅረፍ አዳዲስ እርምጃዎችን እንደሚያስታውቅ ተናግረዋል።

በኔዘርላንድስ የጤና ባለሥልጣናት አገሪቷ ወደ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ልክ እንደ ፈረንሳይ ሁሉ ኦሚክሮን በአገሪቷ ከሌሎች ቫይረሶች በበለጠ ሊታይ ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም ከኅዳር ወር ጀምሮ ምግብ ቤቶች፣ የመጠጥ መሸጫዎች፣ አብዛኞቹ ሱቆች ከምሽቱ 1፡00 እስከ ሌሊቱ 11 ሰዓት ድረስ እንዲዘጉ ታዘዋል። ይህ እርምጃ ከአዲስ ዓመት በፊት ያበቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 14 ድረስ ተራዝሟል።

ኔዘርላንድስ አርብ ዕለት ብቻ ከ15 ሺህ 400 በላይ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በአየርላንድም ከሰኞ ጀምሮ አዳዲስ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ምግብ ቤቶች፣ ምሽት ቤቶች፣ ቲአትር እና ፊልም ማሳያ ቤቶች ምሽት 2፡00 ሰዓት ላይ መዘጋት ይኖርባቸዋል።

ይሁን እንጂ በአየርላንድ አንዳንድ ፖለቲከኞች "ውሳኔው በርካታ ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲሰባሰቡ ያደርጋል" ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።

የስፖርት ቦታዎችም ካላቸው አቅም 50 በመቶ ቀንሰው ታዳሚዎችን እንዲያስተናግዱም ውሳኔ ተላልፏል። የሠርግ ዝግጅቶች ግን ከ100 ባልበለጡ ታዳሚዎች እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እንዲካሄድ ይፈቀዳል።

የአየር ላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በአዲሱ ደንብ ምክንያት የሚጎዱ የንግድ ተቋማትን ለማገዝ የሚረዱ ውሳኔዎችን ሰኞ እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል።