በጀማል ኻሾጂ ግድያ የሚጠረጠር ግሰለብ ፈረንሳይ ውስጥ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ግድያ የሚጠረጠር ግሰለብ ፈረንሳይ ውስጥ አውሮፕላን ለመሳፈር ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ዋለ።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን የሳዑዲ ዜግነት ያለው እና ካሊድ አይደሀ አል-ኦታኢቢ የተባለው ግለሰብ በፓሪስ ዋነኛ አየር ማረፊያ መያዙን እየዘገቡ ይገኛሉ።
ይህ ግለሰብ በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ግድያ በቱርክ መንግሥት ከሚፈለጉ 26 ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።
በፈረንሳይ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ይህ የሳዑዲ ዜግነት ያለው ግለሰብ በይፋዊ ስሙ አውሮፕላን ለመሳፈር ሞክሯል ተብሏል።
ዝነኛው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከሦስት ዓመታት በፊት ገብቶ ደብዛው ጠፍቷል። ይህንንም ተከትሎ ቱርክ ጋዜጠኛው ከሳዑዲ በመጣ ገዳይ ቡድን ተገድሎ አስክሬኑ እንዳይገኝ ተደርጓል ብላ ነበር።
በሳዑዲ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቀው ጋዜጠኛ በቱርክ መዲና በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ የተገደለው በጎርጎሳውያኑ 2018 ነበር።
የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ በኻሾጂ ግድያ የሳዑዲ ከፍተኛ ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት አረጋግጫለሁ ብሎ ነበር።
ጀማል ኻሾግጂ ከመሞቱ በፊት ነዋሪነቱን አሜሪካ ያደረገ ሲሆን ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ይጽፍ ነበር።
ጋዜጠኛው ቆንስላ ውስጥ ከገባ በኋላ መጥፋቱን ተከትሎ የሳዑዲ ባለሥልጣናት እርስ በርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ይሰጡ የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ እንዲያመጣው የታዘዘው ቡድን ተልዕኮው ወዳልሆነ አቅጣጫ አምርቶ ጋዜጠኛው መገደሉን አምኗል።
ከአንድ ዓመት በፊት በጋዜጠኛው ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉ አምስት ግለሰቦችን በሪያድ በተደረገ ምስጢራዊ የፍርድ ሂደት ሞት ተፈርዶባቸዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የዚህን የፍርድ ሂደት "የፍትህ ተቃራኒ" ሲሉ ጠርተውታል።
ጀማል ኻሾግጂ የተከሰተው ምን ነበር?
ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ከጎርጎሳውያኑ 2017 ጀምሮ በስደት በአሜሪካ እየኖረ ነበር።
በጎርጎሳውያኑ ጥቅምት 2018 በኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ያመራውም ቱርካዊት እጮኛው ሃቲስ ሴንጊዝን ለማግባት የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ለመውሰድ ነበር።
መርማሪዎች እንደሚያምኑት እዛው ገድለው አካሉንም እንደ ቆራረጡት ነው። አስከሬኑም ሆነ የተረፈ ነገር አልተገኘም። እጮኛው በወቅቱ ውጭ እየጠበቀች ነበር።
የሳዑዲ ባለስልጣናት በመጀመሪያ ከቆንስላው እንደወጣ የተናገሩ ሲሆን ከዚያ በኋላም በርካታ የሚጣረሱ መረጃዎች ሰጥተዋል።
በኋላ ላይ የወጣው የጋዜጠኛው አሰቃቂ አገዳደል ዝርዝር መረጃ ዓለምን አስደንግጧል።
የተባበሩት መንግሥታትም የሳዑዲው ልዑል ቢን ሳልማንና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግድያው እጃቸው እንዳለበት የታመነ መረጃ እንዳለው ገልፆ ሪፖርት አውትቷል።
ልዑሉ በግድያው ውስጥ እጄ የለበትም ብለው የካዱ ሲሆን ሆኖም "እንደ ሳዑዲ አረቢያ መሪነቴ ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ። በተለይም ገዳዮቹ ለሳዑዲ መንግሥት የሚሰሩ ከመሆናቸው አንፃር" ብለዋል።
















