ፔንግ ሹዋይ፡ በጾታዊ ጥቃት ሳቢያ በቻይና የሚደረጉ የቴኒስ ውድድሮች ታገዱ

ፔንግ ሹዋይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ35 ዓመቷ ፔንግ የቻይናን ከፍተኛ ባለሥልጣን በጾታዊ ጥቃት ከከሰሰች በኋላ ለሦስት ሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍታለች

የቻይናዊቷ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ፔንግ ሹዋይ ጉዳይ ያሳሰበው የሴቶች ቴኒስ ማኅበር (ደብሊውቲኤ) በቻይና የሚደረጉ ሁሉንም ውድድሮች በአስቸኳይ ማገዱን አስታውቋል።

የ35 ዓመቷ ፔንግ የቻይናን ከፍተኛ ባለሥልጣን በጾታዊ ጥቃት ከከሰሰች በኋላ ለሦስት ሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍታለች።

የማኅበሩ ዋና ኃላፊ ስቲቭ ሳይመን እንዳሉት ፔንግ "ነጻ፣ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ለማስፈራሪያ ያልታጋለጠች ስለመሆኑ ከባድ ጥርጣሬዎች አሉን" ብለዋል።

"በጥሩ ህሊና ስፖርተኞቻችን እዚያ እንዲወዳደሩ እንዴት እንደምጠይቅ አይታየኝም" ብለዋል ኃላፊው።

ማኅበሩ በፔንግ ክሶች ዙሪያ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ደጋግሞ ጠይቋል።

የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዣንግ ጋዎሊን በጾታዊ ጥቃት ከከሰሰች በኋላ በፔንግ ጉዳይ ስጋት ተፈጥሯል።

በኅዳር ወር ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባህ ጋር ባደረችው የቪዲዮ ጥሪ "ደህና" መሆኗን ተናግራለች።

ማኅበሩ ግን ቪዲዮው ስለፔንግ "ደህንነት በቂ ማስረጃ አይደለም" ብሏል።

ሳይመን በ2022 በቻይና ውድድሮች ቢደረጉ ተጫዋቾቹ እና ባልደረቦቻቸው ሊያጋጥሟቸው ስለሚችለው አደጋ "በጣም አሳስቦኛል" ብሏል።

"በቻይና ያለው አመራር በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ በምንም መልኩ ሊታመን አይችልም" ብለዋል።

"ታላላቅ ሰዎች የሴቶችን ድምጽ ማፈን እና የጾታዊ ጥቃትን ውንጀላን ማጥፋት ካልቻሉ ማኅበሩ ከተመሠረተበት የሴቶች እኩልነት ዓላማ ትልቅ እንቅፋት ይገጥመዋል።" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"ይህ በማኅበሩ እና በተጫዋቾቹ ላይ እንዲደርስም እንዲሆንም አልፈቅድም" ብለዋል።

እገዳው በሆንግ ኮንግ የሚካሄዱ ውድድሮችንም ያካትታል።

የቀድሞዋ የዓለም ቁጥር አንድ ቴኒስ ተጫዋች እና የማህኅበሩ መስራች ቢሊ ዣን ኪንግ ድርጅቱ ጠንካራ አቋም መያዙን አድንቃለች።

ኪንግ በትዊተር ላይ "ይህ የሴቶች ቴኒስ በሴቶች ስፖርት ውስጥ መሪ የሚሆንበት ሌላው ምክንያት ነው።" ብላለች።

"ደብሊውቲኤ ተጫዋቾቻችንን በመደገፍ በታሪክ ጎን ቆሟል።" ስትልም አክላለች።

የሁለት ጊዜ የዊምብልደን ሻምፒዮናዋ ፔትራ ክቪቶቫ እና የዩኤስ ኦፕን የሩብ ፍጻሜ ተወዳዳሪ የነበረችው ሼልቢ ሮጀርስን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች ለውሳኔው ድጋፋቸውን በትዊተር ገልጸዋል።

የፔንግ ጉዳይ 'ከሥራ ይበልጣል' - ሳይመን

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት በቻይና ምንም አይነት የማኅበሩ ውድድሮች አልተካሄዱም።

ይሁን እንጂ የበላይ አካሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባደረጋቸው ውድድሮች በቻይና ኢንቨስትመንቶች ላይ በእጅጉ ከመንጠላጠሉም በላይ በአገሪቱ በርካታ ውድድሮች እንዲካሄዱ አድርጓል።

ቻይና እአአ በ2019 የውድድር ዓመት ዘመን ውድድሮችን አስተናግዳለች።

የውድድር ዘመኑ ማብቂያ ለሆነው የማኅበሩን የፍጻሜ ውድድርን ጨምሮ በድምሩ 30.4 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት ሰጥታለች።

ሳይመን በቻይና ያለመጫወት የሚያስከትለው የፋይናንስ ችግር እንዳሳሰበው ለቢቢሲ ስፖርት ገልጸው የፔንግ ጉዳይ ግን "ከሥራም የበለጠ ነው" ብለዋል።

"ይህ በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ነገር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"ከጠየቅነው ነገር ርቀን ከሄድን ለዓለም እየነገርነው ያለው ወሲባዊ ጥቃትን እና አሳሳቢነት አለመመልከት በመሆኑ አይሆንም።" ብለዋል።

"እኛ እንዲሆን መፍቀድ የማንችለው እና ከዚያ መሸሽ የማንችለው ነገር ነው" ሲሉም አክለዋል።

በድርብ ውድድር የቀድሞዋ የዓለም ቁጥር አንድ የነበረችው ፔንግ በቻይና ማኅበራዊ ድር አምባ ዌይቦ ላይ ከዣንግ ጋር ጾታዊ ግንኙነት እንድትፈጽም መገደዷን ገልጻለች።

ጽሁፉ ከደቂቃዎች በኋላ የተነሳ ሲሆን ፔንግ ለተወሰነ ጊዜ በአደባባይ አልታየችም።

በርካታ የቴኒስ ተጫዋቾች በትዊተር ላይ #WhereisPengShuai (ፔንግ ሹዋን የታለች) የሚለውን ሃሽታግ ተጠቅመው ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አድርገዋል።

ሳይመን በወንዶች ውድድር ላይ የወንድ ቴኒስ ተጫዋቾች ማኅበር ተመሳሳይ አቋም እንዲይዝ እንደማይጠይቁ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል። የማኅበሩ የበላይ አካል ግን አቋማቸውን እንደሚደግፍ ተናግሯል።

"[የወንዶቹ ማኅበር ውድድሮችን አለማቋረጡ] አቋማችንን የሚጎዳው አይመስለኝም" ብለዋል።

"የእኛ አቋም ለደብሊውቲኤ እና ለሴቶች ስፖርተኞች የተሻለው ነገር ነው እና እኛ በዚያ አቋም እንቀጥላለን።" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

"ሌሎች ለእነሱ ተስማሚ ናቸው ብለው ያሰቡትን ውሳኔ ያሳልፋሉ።" ብለዋል ሳይመን።

የቻይና ባለሥልጣናት የፔንግን ጥያቄዎች "በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት" እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

'ምርጫ የለም'

ሳይመን አክለውም "እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በጣም አዝኛለሁ። የቻይና መሪዎች ግን ማኅበሩ ምንም አማራጭ እንዳይኖረው አድርገዋል።" ይላሉ።

"ቻይና የጠየቅናቸውን እርምጃዎች እስካልወሰደች ድረስ በቻይና ውድድሮችን በማድረግ ተጫዋቾቻችንን እና ሠራተኞቻችንን አደጋ ላይ መጣል አንችልም።" ብለዋል።

ቻይና በጥቅምት ወር ባወጣችው መግለጫ "ሰዎች ሆን ብለው ይህንን ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ ይቅርና [ጉዳዩንም] ማበረታታቸውን ማቆም አለባቸው" ብላለች።

እአአ በ2018 ከመንግሥት ሥራቸው ጡረታ የወጡት ዣንግ ጋዎሊ ስለቀረበባቸው ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

የ2022 የክረምት ኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ በቤጂንግ በየካቲት እና በመጋቢት ወር ሊካሄድ ታቅዷል።