አነስተኛ የማዳበሪያ አቅርቦት ደሃ አገራትን ለምግብ እጥረት እየተጋለጠ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዙሪያ የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት መከሰት የምግብ ዋጋን በማሻቀብ ድሃ አገራትን ለችግር እየዳረገ ነው ሲሉ የግዙፉ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኃላፊ ተናገሩ።
በዘርፉ ዝና ገናና ስም ያለው ያራ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስቬን ቶሬ ሆልሴተር የነዳጅ ዋጋ መጨመር የማዳበሪያ ወጪን ከፍ በማድረጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች ለምርት ሂደት ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ይጠቀማሉ።
ሆልሰተር ያራ በነዳጅ ዋጋ ንረት ምክንያት የተወሰነ ምርት ለማቋረጥ መገደዱን እና ይህም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ታዳጊ አገራት በእጥረቱ ክፉኛ እንደሚጎዱ እና የሰብል ምርት እየቀነሰ በተቃራኒው የምግብ ዋጋ እየጨመረ እንደሚሄድም አስረድተዋል።
"በጣም አስፈሪ ነው። የምግብ እጥረት ቀውስን እየተጋፈጥን ነው። ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በጣም እየተጎዱ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በመላው ዓለም የምግብ ዋጋ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ የብዙ ሰዎችን ኪስ ያራቁታል። ለአንዳንድ ሰዎች ግን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገራት የኪስ መራቆት ብቻ ሳይሆን የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ሆልሰተር የማዳበሪያ ምርት አቅርቦት ማነስ ምንነትን ሲያስረዱ፤ የማዳበሪያ እጥረት ካለ በታዳጊ አገራት ያሉ ገበሬዎች በበቂ ሁኔታ መዝራት አይችሉም ማለት ነው። ይህም ከእርሻ ቦታ የሚሰበሰበውን ሰብል ያነሰ እንዲሆን ያደርጋል።
እንደ በቆሎ እና ስንዴ ያሉ የሰብል ምርቶችን ለማሳደግ አርሶ አደሮች ማዳበሪያን ይጠቀማሉ የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በብዙ የማዳበሪያ ምርቶች ውስጥ የሚገኘው 'አሞኒያ' የተባለው ግብዓት የሚፈጠረው በውሃ ኃይል ወይም በተፈጥሮ ጋዝ ላይ ተመሰረቶ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ የጨመረው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ፍላጎት በመጨመሩ ነው። ይህም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ኢኮኖሚው ዳግም ሲከፈት የንፋስ ወይም ዝናብ ኃይልን ለታዳሽ ኃይል መጠቀም መቀነስን ያካትታል።
ይህም የአሞኒያን ዋጋ በማናሩ ማዳበሪያ የማምረቻ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል።
ሆልሰተር ሁኔታው "በጣም ተለዋዋጭ ነው" ያሉ ሲሆን "በከፍተኛ ደረጃ ረሃብን ለማስወገድ" የዓለም ምግብ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ዓመት ድርጅታቸው 40 ሺህ ቶን ማዳበሪያ በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ አገራት መለገሱን የተናገሩት ኃላፊው፤ በልገሳው ምክንያት በአገራቱ የሚገኙ አነስተኛ እርሻዎች የሰብል ምርት በሦስት እጥፍ እንዲጨምሩ አድርጓል ብለዋል።
ይህም "ማዳበሪያ ስላለው አስፈላጊነት ብዙ የሚናገር" ነው ሲሉ አክለዋል።












