ሩሲያዊያን ተሳታፊ የሆኑበት የመንግሥት ግልበጣ ተሲሯል ስትል ዩክሬን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዲሚይር ዜሌኒስኪይ የሩሲያ "ወኪሎች" በቀጣይ ሳምንት የመንግሥት ግለበጣ ለማድረግ እያሴሩብኝ ነው አሉ።
ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ ይህን ያሉት ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ጦሯን እያደረጀች ባለበት ወቅት ነው።
የሩሲያን ሰሞናዊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተመለከቱ ዩክሬንን የመውረር እቅድ ሳይኖር አይቀርም በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ነገር ግን የሩሲያ መንግሥት ቃል አባይ በበኩላቸው፤ ሩሲያ በዩክሬን ጉዳይ "ጣልቃ የመግባት ዕቅድ የላትም" ብለዋል።
ሞስኮ ከዚህ በተጨማሪም ወታደሮቿን በድንበር አቅራቢያ ማሰባሰቧ "አሳሳቢ ነው" መባሉን አጣጥላለች።
አርብ ዕለት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገራት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ ሩሲያ በዩክሬን ላይ አንዳች የኃይል እርምጃ ብትወስድ "ዋጋ ያስከፍላታል" ሲሉ ማሰጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝደንት በበኩላቸው ከሩሲያ በኩል አደጋኛ የሆነ ዛቸው እየመጣ ነው ይላሉ። "ምልክት ነው . . . ሊባባስ ይችላል። ነገ ላይ ጦርነት ሊኖር እንደሚችል ዛሬ ላይ ስጋት አለ። ተባብሶ ለሚቀጥል ነገር ዝግጁ ነን" ብለዋል።
አብዛኛው የሩሲያ ጦር እአአ 2014 ላይ ከዩክሬን በኃይል በያዘችው ክሬሚያ ግዛት ውስጥ ይገኛል። በቅርቡ ደግሞ የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን ወደሚገኘው ዶንባስ ግዛት እየተጠጋ ይገኛል።
የመፈንቅለ መንግሥት ክስ
"በእኛ አገር (ዩክሬን) ኅዳር 22 ላይ መፈንቅለ መንግሥት እንደሚኖር መረጃ ደርሶኛል" ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዜሌኔስኪ እንደሚሉት እርሳቸውን የሚቃወም እና ባለሃብት የሆነው ሪናት አክሜቶቭ የተባለው ግለሰብ "በዩክሬን መንግሥት ላይ በተከፈተው ጦርነት ውስጥ ተጎትቶ ገብቷል" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ በመንግሥታቸው ላይ ተወጥኗል ባሉት ሴራ ውስጥ እነማን ተሳታፊ እንደሆኑ ባይዘረዝሩም፤ ባለሃብቱ ግለሰብ አውቀውም ሆነ ሳይወቁ በዚህ ዕቅድ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል ብለዋል።
ሪናት አክሜቶቭ ባወጡት መግለጫ፤ የፕሬዝደንቱን ውነጀላ "ሐሰት" በማለት በዚህም መበሳጨታቸውን ገልጸዋል።












