ኮቪድ 19፡ እስራኤል በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት በውጭ ዜጎች ላይ የጉዞ እገዳ ልትጥል ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል አዲስ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ዝርያ ተከትሎ የውጭ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ለ14 ቀናት የጉዞ ገደብ ልትጥል መሆኑንና የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ በደህንነት መሥሪያ ቤት ክትትል ልታደርግ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
እገዳው በሙሉ ካቢኔው ከጸደቀ በኋላ ከእሁድ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ በተገኘውና ተላላፊ በሆነው ኦሚክሮን ቫይረስ የተያዘ አንድ ሰው ማግኘቷን አረጋግጣለች።
በርካታ አገራትም ወደ ደቡብ አፍሪካና ጎረቤት አገሮቿ የሚደረግ ጉዞን አግደዋል።
ደቡብ አፍሪካ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ 'ኦሚክሮን'ን በማግኘቷ በመወደስ ፈንታ እየተቀጣሁ ነው ስትል ቅሬታዋን አሰምታለች።
የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱ ዝርያ " እጅግ አሳሳቢ ነው" ሲል ያስጠነቀቀ ሲሆን የወጡ መረጃዎችም ቫይረሱ እንደገና የመያዝ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያመለክቱ ገልጿል።
ይሁን እንጂ ድርጅቱ አገራት "የአደጋውን ሁኔታ እና ሳይንስን መመልከት" አለባቸው ሲል አገራት የጉዞ እገዳዎችን በችኮላ እንዳይጥሉ አሳስቧል።
የእስራኤል የኮሮናቫይረስ ካቢኔ ቅዳሜ እለት በነበራቸው ስብሰባ አዲስ በሚጣሉ ገደቦች ላይ የተስማሙ ሲሆን በትልቁ ካቢኔ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል።
ካቢኔው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ ከማገድ በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ክትባት የወሰዱ እስራኤላውያን ወደ አገሪቷ ሲገቡ ለሦስት ቀናት አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይጠየቃሉ።
ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ደግሞ ለ7 ቀናት ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል።
ከዚህም ባሻገር ካቢኔው በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች በእስራኤል ሺን ቤት የደህንነት ኤጀንሲ ክትትል እንዲደረግባቸው ውሳኔ አሳልፏል።
ቅዳሜ እለት እስራኤል 50 የአፍሪካ አገራትን 'በቀይ መዝገብ' ውስጥ ከትታለች።
ከእነዚህ አገራት የሚመለሱ እስራኤላውያን መንግሥት ፈቃድ በሰጣቸው ሆቴሎች ራሳቸውን ማቆየትና የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብሏል-ካቢኔው።
እስራኤል የውጭ ዜጎች ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ የጣለችው አርብ እለት ነው።
እንደ አሜሪካው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በእስራኤል ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ ከ1.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከ8 ሺህ 100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።












