የኮሮናቫይረስ ወረርሽን መከሰት የጠጪዎችን ቁጥር ከፍ አድርጎት ይሆን?

የወይን መጠጥ ዓይነቶች

የፎቶው ባለመብት, The wine society

ሳም ኩፐር የጀመረው የንግድ ሥራ የጥንታዊ አኗኗር ዘይቤን ከኢንተርኔት ከተገኙ መረጃዎች ጋር በማጣመር ነው።

ጥንታዊ ምዕራባዊ ዌልስ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ማርን በተፈጥሯዊ እርሾ አማካይነት ከውሃ ጋር በመቀላለቅ 'ሚድ' የተሰኘውን የአልኮል መጠጥ ይሰሩ ነበር።

ሳም ለሚያዘጋጀው ጥንታዊ የአልኮል መጠጥ ግብአት የሚሆነውን ማር ለማግኘት ደግሞ የራሱን የንብ ቀፎ ነው የሚጠቀመው። በመላው ዌልሰም በ50 የተለያዩ አካባቢዎች ከ500 በላይ የንብ ቀፎዎች አሉት።

በአውሮፓውያኑ 1999 የተጀመረው ይህ የንግድ ሥራ ታዲያ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ካጠቃ በኋላ እንደ አዲስ መነቃቃቱን ሳም ይገልጻል።

"ከመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደብ ጀምሮ በበይነ መረብ አማካይነት እኔ የምሰራውን አልኮል የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል" ይላል ሳም ኩፐር።

"በርካታ ሰዎች ሚድ የተባለውን መጠጥ ከጥንታዊ ሰዎች ጋር ነው የሚያይዙት። እውነታውም እንደዚያው ነው። ጥንታዊ መጠጥ ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል።"

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ከአልኮል ጋር በተያያዘ ሁለት አይነት ሀሳቦች በብዛት ይነሳሉ። ሰዎች ቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከመቀመጥ የተነሳ የአልኮል ፍጆቻቸው ጨምሯል የሚለው የመጀመሪያው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ሰዎች ወደ መጠጥ ቤቶች ስለማይሄዱ የአልኮል ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል የሚል ነው።

ነገር ግን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ወረርሽኙን ተከትሎ ሰዎች ከዚህ በፊት ሞክረዋቸው የማያውቋቸውን የመጠጥ አይነቶች እንዲሞክሩ እያደረገ መሆኑ ነው።

ከዚህ በፊት በመላው ዓለም እምብዛም እውቅና ያልነበራቸው የመጠጥ አይነቶችና ወይኖች በበይነ መረብ አማካይነት ትልቅ እውቅና እያገኙና የተጠቃሚያቸው ቁጥር እየጨመረ ነው።

ኒው ዮርክ ውስጥ በቤተሰብ የሚተዳደር የአልኮል መሸጫ ኃላፊ የሆነው ጆናታን ጎልደስቲይን እንደሚለው ወረርሽኙነት ተከትሎ ሰዎች አዳዲስ ነገሮችን እየሞከሩ ነው።

"ሁሉም ነገር ሲዘጋጋና ሰዎች መሄጃ ሲያጡ የተለያዩ ነገሮችን እየሞከሩ ነበር። ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን ልክ እንደ መጠጥ ቀጂ በመሆንና የተለያዩ መጠጦችን በማቀላቀል እራሳቸውን በሥራ ሲጠምዱ ነበር። ይህን ተከትሎ ከእኛ የመጠጥ መሸጫ የተለያዩ አይነት መጠጦችን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል" ይላል።

ነገር ግን ጆናታን እንደሚለው ለኮሮናቫይረስ የሚሆን ክትባት መምጣቱን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደቦች መላላትና ሰዎች ወደቀደመው የህይወት ዘይቤ መመለስን ተከትሎ ገበያቸው በእጅጉ ቀንሷል።

መጠጦች

የፎቶው ባለመብት, AFON MEL

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ግዙፍ የወይን ሻጭ 'ዋይን ሶሳይቲ' እንደሚለው የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የአውስትራሊያ እና የግሪክ ወይኖች ተፈላጊነት በጣም ጨምሯል።

"በአውሮፓውያኑ 1874 ዋይን ሶሳይቲ ሲመሰረት የመጀመሪያው ዓላማው ብዙም የማይታወቁ የወይን አይነቶችን አልያም በእኛ አገር ብዙ ተጠቃሚ የሌላቸውን ወይኖች ማስተዋወቅ ነበር" ይላል የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢዋን ሙሬይ።

"ይህ ዓላማችን አሁንም አለ። ከመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደብ በኋላ የእነዚህ የወይን አይነቶች ፍላጎት ጨምሯል። በዚህ ምክንያት በጣም የተጠቀሙት ሁለት አገራት ደግሞ ግሪክና አውስትራሊያ ናቸው።"

የዋይን ሶሳይቲ የግሪክ ወይኖች ሽያጭ በአውሮፓውያኑ 2019 ዓ.ም. 500 ሺህ ፓውንድ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ መጨመር አሳይቶ 700 ሺህ ፓውንድ ደርሷል። በያዝነው 2021 ደግሞ በእጅጉ ጭማሪ አሳይቶ 2 ሚሊየን ፓውንድ ደርሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውስትራሊያ ወይኖች ደግሞ 2019 ላይ ከነበረው 900 ሺህ ፓውንድ ሽያጭ በ2020 ወደ 1.4 ሚሊየን ፓውንድ ከፍ ያለ ሲሆን በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ደግሞ 2.1 ሚሊየን ደርሷል።

የግሪክ ወይኖች ተፈላጊነት የጨመረው ምናልባት ሰዎች ከወረርሽኙ በፊት ወደ ግሪክ ሄደው ለመዝናናት አስበው የነበሩ ሰዎች በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ሌላው ቢቀር ግሪክ ባንሄድ እንኳን የግሪክ መጠጦችን እንቅመስ በሚል ሊሆን እነደሚችል መገመት ቀላል ነው።

ሳም ኩፐር ዘጠኝ የሚድ አይነቶችን የሚያመርት ሲሆን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ጣዕም ያላቸው ናቸው። ይህ መጠጥ በውስጡ 13 በመቶ የአልኮል መጠን ያለው ሲሆን መቀዝቀዝ አያስፈልገውም።

ከዚህ በተጨማሪም 'ሴሽን ሜድስ' የተባሉ ቀለል ያለ የአልኮል መጠን ያለቸውና ልክ እንደ ቢራ ደጋግሞ ለመጠጣት የሚያስችሉ መጠጦችንም ያዘጋጃል።

"በዓመት ቢያንስ ከሁሉም አይነት መጠጦች እስከ 30 ሺህ ሊትር ድረስ እንሸጣለን። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአልኮል ሽያጭ ገበያችንን በእጅጉ ነው የጨመረልን" ይላል ሳም።

"ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እንደ ጌም ኦፍ ትሮንስ እና ቫይኪንግስ ያሉ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች የእኛን መጠጦች ተፈላጊነት ጨምረውልናል።"