ኮሮናቫይረስ፡ መማሪያ ክፍሎችን ወደ ዶሮ ማርቢያነት የለወጠው ኮሮናቫይረስ

በቀድሞው የትምህርት ክፍል ውስጥ ዶሮ ማርባት የጀመረው ጆሴፍ
የምስሉ መግለጫ, በቀድሞው የትምህርት ክፍል ውስጥ ዶሮ ማርባት የጀመረው ጆሴፍ

በኬንያ ለወራት የተዘጉት ትምህርት ቤቶች ለሌላ አገልግሎት እየዋሉ ነው።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ ወራቶች ተቆጥረዋል። በአንዳንድ አገራት ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ቢሆንም ፤ ቀድመው የከፈቱት ደግሞ የቫይረሱ ሥርጭት በመስፋፋቱ እንደገና እየዘጉ ነው።

ወረርሽኙ ግራ አጋቢ ሆኗል። በኬንያም ትምህርት ቤቶች እስከ መጭው ጥር ወር ድረስ አይከፈቱም ተብሏል። ይህም በርካታ የግል ትምህርት ቤቶችን ህልውና ፈታኝ አድርጎታል።

ይህንን ተከትሎም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ወደ ሌላ ተግባር ተለውጠዋል።

በኬንያ ካሉ የግል ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ምዌ ብሬትረን፤ መማሪያ ክፍሎች ውስጥ ይሰማ የነበረው የተማሪዎች የቀለም ዜማ በዶሮ ጫጩቶች ጩኸት ተሞልቷል።

በጥቁር ሰሌዳው ላይ ይፃፉ የነበሩ የሒሳብ ስሌቶችም፤ አሁን የበሽታው ክትባት መቼ ሊገኝ ይችላል በሚል መርሃ ግብር ተተክተዋል።

የማዕከላዊ ኬንያ ትምህርት ቤት ባለቤት ጆሴፍ ሜና፤ በወረርሽኙ ሳቢያ ትምህርት ቤቱ በመዘጋቱና የተወሰነ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ወደ ዶሮ እርባታ ፊቱን አዙሯል።

መጋቢት ወር ላይ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሲነገር፤ ውሳኔው የባንክ ብድር ለሚከፍለው ጆሴፍ ዱብዳ ነበር የሆነበት።

መጀመሪያ ላይ በሁኔታው ሰማይ ምድሩ የተገለባበጠ ያህል ቢሰማውም በኋላ ላይ ኑሯቸውን የሚደጉም አንድ ነገር መሥራት እንዳለባቸው መወሰናቸውን ጆሴፍ ይናገራል።

የግል ትምህርት ቤቶች እንደመሆናቸው ገቢያቸው በተማሪዎች ክፍያ ላይ የተመሰረተ ነው፤ በመሆኑም ትምህርት በመዘጋቱ ለሰራተኞቻቸው መክፈል እንዳይችሉ ሆነዋል።

የተማሪዎች የመጫወቻ ሜዳ የተለያዩ አትክልቶች እየተተከሉበት ነው
የምስሉ መግለጫ, የተማሪዎች የመጫወቻ ሜዳ የተለያዩ አትክልቶች እየተተከሉበት ነው

በዚህም በርካታ መምህራን ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ገጥሟቸዋል።

በማዕከላዊ ኬንያ የሚገኘው ሌላኛው ትምህርት ቤት ሮካ ፕሪፓራቶሪም በዚህ ችግር የተነሳ የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ ወደ እርሻ ለውጧል።

ትምህርት ቤቱን ከ23 ዓመታት በፊት የመሰረቱት ጀምስ ኩንጉ፤ “ነገሮች እንደዚህ አስከፊ ሆነው አያውቁም” ብለዋል።

በግቢው ውስጥ የተማሪዎች መጫዋቻ ሜዳ የነበረው፤ አሁን የጓሮ አትክልት ማብቀያ ሆኗል።

“ሁኔታው በሥነ ልቦናም እጅግ ጎድቶናል፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረጋችን ቢያንስ እንዳንሰላች ረድቶናል፤ ይህም እንደ አንድ የሥነ ልቦና ሕክምና ነው” ብለዋል ጀምስ።

እንደ የኬንያ የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ከሆነ በኦንላይን ትምህርት መስጠት የቻሉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

እነርሱም ቢሆኑ የሚያገኙት ገቢ ለመምህራኑ መሰረታዊ ፍጆታቸውን እንኳን የሚሸፍን አይደለም።

በግል ትምህርት ቤቶች ከሚሰሩ ከ300 ሺህ በላይ ሰራተኞች 95 በመቶ የሚሆኑት ያለ ደመወዝ ፈቃድ እንዲወጡ መደረጋቸውንም የማህበሩ ሊቀመንበር ፒተር ንዶሮ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ 133 ትምህርት ቤቶች ጭራሹኑ ለመዝጋት ተገደዋል።

የመምህራን እጣ ፈንታሁለቱ ትምህርት ቤቶች አማራጭ የገቢ ምንጭ ቢያገኙም፤ ባለቤቶቹ ግን ለአምስት ወራት ያለ ክፍያ ስለቆዩት መምህራን እጣ ፈንታ ተጨንቀዋል።

አንዳንድ መምህራን ‘የሚሰራ ነገር ካለ’ ሲሉ የሚጠይቋቸው መምህራን መኖሩንም የሚናገሩት ጆሴፍ፤ እንኳን ለእነርሱ ለመትረፍ ራሳቸውንም ለመመገብ በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት በርካቶች ወደ ሌላ አማራጭ የሙያ ዘርፍ እየተሰማሩ ነው።

የግል ትምህርት ቤቶች ማህበሩ እያጋጠማቸው ላለው የገንዘብ ችግር መንግሥት በአጠቃላይ 65 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ይፈልጋል።

የገንዘብ ድጋፉ ካልተደረገላቸው ግን “አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ባሉበት መቆየት አይችሉም” ብሏል።

የትምህር ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶቹ ብድር በማዘጋጀት ድጋፍ ቢያደርግም፤ የማህበሩ ሊቀመንበር ግን ይህ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ሊታደግ አይችልም የሚል ስጋት አላቸው።

ኮሮና
Banner