የሩሲያዊያን የአልኮል መጠጥ ፍጆታ መቀነሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያዊያን የአልኮል መጠጥ ፍጆታ ከአውሮፓዊያኑ 2003 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ 43 በመቶ ያህል መቀነሱን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።
ለአልኮል ፍጆታቸው መቀነስ ምክንያት ነው የተባለው የሩሲያ መንግሥት የወሰደው ጥብቅ ቁጥጥርና ዜጎቹ ወደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመሸጋገራቸው እንደሆነ ተነግሯል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የአልኮል ፍጆታ መጠን የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ከሚኖረው እድሜ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት አለው።
ከዚህ ቀደም ሩሲያ በዓለማችን በጣም በርካታ ጠጪዎች ካሉባቸው አገራት አንዷ ነበረች።
በሩሲያ የአልኮል መጠጥ ፍጆታ በተለይ አምራች ለሆኑ ወጣት ወንዶችን ሞት ከሚያፋጥኑ ምክንያቶች መካከል አንዱ ተደርጎም ይወሰድ እንደነበር ሪፖርቱ ያስረዳል።
ይሁን እንጂ ከ2003 እስከ 2018 ድረስ ባሉት ጊዜያት የአልኮል ፍጆታና የሞት መጠን ቀንሷል። ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እንዲሁ።
ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ታሪክ በአስገራሚ ሁኔታ የሩሲያዊያን የመኖሪያ አማካይ እድሜ ለወንዶች 68 ዓመት ለሴቶች ደግሞ 78 ዓመት እንደደረሰ ተገልጿል።
የአልኮል ቁጥጥር እርምጃዎችን ያስተዋወቁት የቀድሞ የአገሪቷ ፕሬዝደንት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ሲሆኑ የማስታወቂያ ሕጎችን በማውጣት፣ በአልኮል ምርቶች ላይ ግብር በመጨመር እና አልኮል መጠጥ የሚሸጥበትን ሰዓት በመገደብ ቁጥጥር ሲደረግ ቆይቷል።














