'ኦሚክሮን' ተብሎ የተሰየመው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ 'አሳሳቢ' ነው ተባለ

የምትከተብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ አገራት ውስጥ እየተገኘ ያለውን አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ "አሳሳቢ" ብሎ ያወጀ ሲሆን ስያሜውንም 'ኦሚክሮን' ብሎታል።

ይህ የፃይረስ ዝርያ በብዙ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለፈ ሲሆን ማስረጃዎች ቀደም ሲል ተይዘው የነበሩ ሰዎች በቫይረሱ የመያዝ ምጥኔን እንደሚጨምር ይጠቁማሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ይህ የኮሮናቫይረስ ዝርያን በተመለከተ ከሁለት ቀናት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በቦትስዋና፣ በቤልጂየም፣ በሆንግ ኮንግ እና በእስራኤልም ተገኝቷል።

በዚህም ሳቢያ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አገራት ወደ ደቡብዊ የአፍሪካ ክፍል የሚደረጉ ወይም ከዚያ የሚነሱ ጉዞዎች ላይ ገደብ ጥለዋል ወይም ለማገድ ውሳኔ እያሳለፉ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናሚቢያ፣ ከዚምባብዌ፣ ከቦትስዋና፣ ከሌሴቶ እና ከኤስዋቲኒ የሚነሱ ተጓዦች የዩናይትድ ኪንግደም ወይም የአየርላንድ ዜጎች ወይም ነዋሪዎች ካልሆኑ በስተቀር ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ አግዳለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ዚምባብዌ፣ ናሚቢያ፣ ሌሶቶ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሞዛምቢክ እና ማላዊ የሚነሱ በረራዎች እንደሚታገዱ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ይህንን እርምጃ ቀደም ብሎ የወሰደው ሲሆን እገዳው ከሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

ብራዚል እና አውስትራሊያም የጉዞ እገዳዎችን አውጥተዋል።

"መጥፎ ዜና ቢሆንም የምጽአት ቀን አይደለም"

የዓለም ጤና ድርጅት ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በሁሉም የደቡብ አፍሪካ አገራት ግዛቶች ውስጥ እየጨመረ የመጣ ይመስላል ሲል ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

"ይህ ዝርያ ብዙ አይነቶች አሉት አንዳንዶቹም አሳሳቢ ናቸው" ብሏል።

ዝርያው ኦሚክሮን ተብሎ ከመሰየሙ በፊት 'ቢ.1.1.529' በሚል ነበር የሚታወቀው። "ዝርያው መኖሩ በመጀመሪያ የተረጋገጠው ከሁለት ሳምንት በፊት ከተሰበሰበ ናሙና ነው" ሲልም አክሏል መግለጫው።

ሳይንቲስቶች ዝርያው በምን ያህል ፍጥነት እንደሚተላለፍ ለማወቅ እየሰሩ ሲሆን ተፅእኖውን ለመረዳት ጥቂት ሳምንታት ይፈጃል ተብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣናት አሁን በአገልግሎት ላይ ያሉት የኮቪድ ክትባቶች በአዲሱ ዝርያ ላይ "በእርግጠኝነት" እምብዛም ውጤታማ እንደማይሆኑ እየተናገሩ ነው።

ነገር ግን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ስትራክቸራል ባዮሎጂስት ፕሮፌሰር ጄምስ ናይስሚት "ይህ መጥፎ ዜና ነው፤ ሆንም የምጽአት ቀን አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በጥድፊያ የጉዞ ገደቦችን የሚጥሉ አገራትን ያስጠነቀቀ ሲሆን "ስጋትን መሰረት ያደረገ እና ሳይንሳዊ አካሄድን" በመከተል መወሰን አለባቸው ብሏል።

ከዚህ ምክር በተቃራኒ ግን ዩኬ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በተጨማሪ ሌሎችም አገራት እገዳዎች እየጣሉ ነው።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስትር ጆ ፋህላ የበረራ እገዳው "ምክንያታዊ አይደለም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"የአንዳንድ አገራት የጉዞ እገዳን እና መሰል እርምጃዎች በዓለም ጤና ድርጅት ከሚታወቀው ደንብ እና መመዘኛዎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጻረር ነው" ብለዋል።