አሜሪካ ከ20 ወራት በኋላ ድንበሯን ለተከተቡ ተጓዦች ልትከፍት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስ ለ20 ወራት የጣለችውን የጉዞ እገዳን በማንሳት ለተከተቡ የውጭ አገር ጎብኚዎች ከዛሬ ጀምሮ ድንበሯን ትከፍታለች።
እገዳው በኮቪድ-19 ምክንያት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጥሎ ነበር።
ሙሉ ለሙሉ ለተከተቡ፣ ከበረራ በፊት ከኮቪድ-19 ነጻ ሰርተፊኬት ማቅረብ ለሚችሉ እና ንክኪያቸውን ለሚያሳውቁ ሰዎች የጉዞ እገዳው ተነስቷል።
ይህን ተከትሎ አየር መንገዶች በተጓዦች እንደሚጥለቀለቁ ይጠበቃል።
በፓሪስ የሚገኘው የጄትሴት ቮዬጅስ የጉዞ ወኪል ኃላፊ ዤሮም ቶማን ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ጥሩ ስሜት ይፈጥራል። ጥሩ ስሜት ይፈጥራል!" ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የሚቆረጥ የአየር ቲኬት ብዛት ላይ "አስደናቂ ለውጥ" ማየታቸውን ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የአሜሪካ ድንበሮች እአአ በ2020 መጀመሪያ ላይ ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ተዘጉ። ቆይቶ እገዳው በሌሎች አገራት ላይም ተፈጻሚ ሆኖ ነበር።
ክልከላው ከዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች በርካታ የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢራን እና ብራዚል አሜሪካዊ ያልሆኑ ዜጎች እንዳይገቡ ይከለክል ነበር።
በአዲሱ ሕግ የውጭ ሃገር ተጓዦች ከበረራ በፊት የክትባት ማረጋገጫን ማሳየት፣ ከጉዞው በፊት ባሉት ሦስት ቀናት ኮቪድ-19 ተመርምረው ነጻ መሆናቸው ማሳየት እና የንክኪ መረጃቸውን ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። እራስን ለይቶ ማቆየት ግን አይጠበቅባቸውም።
የ63 ዓመቷ እንግሊዛዊት አሊሰን ሄንሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ልጄን ማየት ብቻ ነው የምፈልገው" ብለዋል።
ሄንሪ በ20 ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸውን ለማየት ሰኞ ወደ ኒው ዮርክ ለመብረር አቅደዋል።
አሜሪካ ከጎረቤት ካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነወትን የመሬት ድንበሮች ሙሉ ለሙሉ ለተከተቡ ሰዎች በድጋሚ ትከፍታለች።
በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋ የሰነቁ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሜክሲኮን ከአሜሪካ ጋር በሚያዋስኗት የድንበር አካባቢዎች ደርሰዋል።
የዩናይትድ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዓለም አቀፍ መንገደኞችን 50 በመቶ ጭማሪ እንደሚጠብቅ ሲገልጽ የዴልታ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢድ ባስቲያን ደግሞ ተጓዦች ወረፋ ሊገጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ባስቲያን "መጀመሪያ ላይ ትንሽ አስቸጋሪ ይሆናል። በሚያሳዝን ሁኔታ ሰልፎች እንደሚኖሩ ላረጋግጥ እችላለሁ" ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት አሜሪካዊያን ተጓዦች ከግንቦት ጀምሮ ወደ አባላት አገራት እንዲገቡ ሲፈቅድ፤ እንግሊዝ በበኩሏ ከአሜሪካ የመጡ ጎብኚዎች እንዲገቡ የፈቀደችው ሰኔ 28 ነበር።












