የኮቢ ብራያንት ባለቤት ኮቢ መሞቱን መጀመሪያ የሰማችው ከማኅበራዊ ሚዲያ እንደነበር ገለጸች

ቨኔሳ እና ኮቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮቢ ብራያንት ባለቤት ቨኔሳ ብራያንት ባለቤቷ መሞቱን መጀመሪያ የሰማችው በማኅበራዊ ሚዲያ እንደነበር ገለጸች።

"RIP Kobe" (ኮቢ ነፍስህ በሠላም ትረፍ) የሚል የስልክ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች መልዕክት ጠቋሚ (ኖቲፊኬሽን) ሲደርሳት ነበር ባለቤቷ መሞቱን የተረዳችው።

የቅርጫት ኳስ ኮከኩ ኮቢ እአአ ጥር 2020 በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ ከ13 ዓመቷ ሴት ልጁ ጂያና እና ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር ሕይወቱ አልፏል።

ቨኔሳ ብራያንት በቸልተኝነት እና ግላዊነትን ባለመጠበቅ ምክንያት የሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያን ከሳለች።

ኃላፊዎቹ የኮቢ እና የጂያናን አስከሬን ጨምሮ የአደጋውን አስከፊ ፎቶዎች አጋርተዋል ስትል ትከሳለች።

ቨኔሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አደጋው እንዴት እንዳወቀች ተጠይቃ ባለቤቷ እና ሴት ልጃቸው የሄሊኮፕተር አደጋ እንደደረሰባቸው ከቤተሰቡ ረዳት እንደተነገራት አስታውቃለች። ነገር ግን አምስት ሰዎች በሕይወት መትረፋቸው ስለተነገራት በሕይወት ከተረፉት መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰቧን ተናግራለች።

ከዚያ በኋላ መልዕክቶች በስልኳ ይደርሷት ጀመር።

ቨኔሳ "ስልኬን ይዤው ነበር። ምክንያቱም ለባለቤቴ ለመደወል እየሞከርኩ ነበር። RIP Kobe የሚሉ ማሳወቂያዎች ስልኬ ላይ ይጎርፉ ጀመር" ስትል ታስታውሳለች።

አክላም "ያለ ባለቤቴ እና ልጄ ሕይወቴ መቼም እንደ ቀድሞው አይሆንም" ብላለች።

በመጋቢት ወር ቨኔሳ የአደጋውን አስከፊ ፎቶዎችን አጋርተዋል ያለቻቸውን የሎስ አንጀለስ የፖሊስ መኮንኖችን ስም ይፋ አድርጋለች።

ከፖሊስ መኮንኖች መካከል አንዱ የኮቢ ብራያንት አስከሬን ፎቶ ለመጠጥ ቤት አሳላፊ ሲያጋራ ሌሎቹ ደግሞ ሕይወታቸው ያለፈ ልጆችን፣ የወላጆችን እና የአሰልጣኞችን ፎቶዎች አሰራጭተዋል።

የሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር እንደዘገበው፤ የፖሊስ የውስጥ ምርመራ እንደሚያሳየው ባለሥልጣናት የተጎጂዎችን ፎቶዎች አጋርተዋል።

ቨኔሳ "ዛሬ እዚህ መጥቼ ለተጠያቂነት መታገሌ ተገቢ አይመስለኝም። ምክንያቱም ማንም ሰው እንደዚህ ዓይነቱን ስቃይ እና የቤተሰቡን ፍርሃት መታገስ የለበትም። ፎቶዎቹ መጋራታቸው ተገቢ አይደለም" ብላለች።

ቨኔሳ ባለቤቷ እና ሴት ልጃቸው አደጋው ሲደርስ የለበሱትን ልብስ እንዳስቀመጠችው ተናግራለች።

"አንድ ሰው እንዴት በጣም ጨካኝ ሊሆን እንደሚችል እና ለእነሱ ወይም ለጓደኞቻችን ምንም ደንታ እንደሌለው መገመት ይከብዳል። የመንገድ እንስሳት የሆኑ ይመስል ፎቶዎቻቸውን አጋርተዋል" ብላለች።

ቨኔሳ በአደጋ ቦታው ማንም ፎቶ አለማንሳቱ እንዲረጋገጥ መጠየቋን የፖሊስ መኮንን አሌክስ ቪላኑዌቫን ተናግረዋል።

የፖሊስ መምሪያው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ባለው ክስ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።