ኡጋንዳ ካምፓላ ውስጥ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት አንድ ሰው ተገደለ

የፖሊስ መኪና

በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ፍንዳታው ቅዳሜ ምሽት በአንድ መጠጥ ቤት የደረሰ ሲሆን የ20 ዓመት አስተናጋጅን ሕይወት ነጥቋል። ሰዎች በፍርሃት ተሞልተው ጎዳና ላይ ታይተዋል።

ሦስት ተጠርጣሪዎች የመጠጥ ቤቱ ደንበኛ መስለው ገብተው ቦንቡን ጠረጴዛ ስር ማስቀመጣቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን በኋላ ላይ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

ፍንዳታው የደረሰው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኡጋንዳ የሽብር ጥቃት ሊደረስ ይችላል በሚል ማስጠንቀቂያ ከሰጠ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

እንዲህ ያለ ጥቃት ብዙም በማይደርስባት ኡጋንዳ "አሸባሪዎች ጥቃቶችን ለመፈጸም የመሞከር ዕድላቸው ከፍተኛ ነው" ስትል ነው ዩኬ ዜጎቿን ያስጠነቀቀችው።

ምግብ ቤቶችን እና ቡና ቤቶችን ጨምሮ ሕዝብ በሚበዘባቸው ቦታዎች እንዲጠነቀቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ፖሊስ ከፍንዳታው በኋላ በከተማዋ ዳርቻ በሚገኘው እና በብዛት መኖሪያ ቤቶች ያሉበትን የመዝናኛ ስፍራ ከቧል።

የአካባቢው ከንቲባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሕብረተሰቡ በፍርሃት ተውጦ ጥቃቱ ለምን ሰፈሩ ላይ እንደተነጣጠረ ጠይቋል ብለዋል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ፍሬድ ኤናንጋ እንዳሉት፤ ጥቃት አድራሾቹ ጠረጴዛው ስር የፕላስቲክ ከረጢት ከማስቀመጣቸው በፊት ምግብ እና መጠጦች አዘው ነበር። ከፍንዳታው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቦታውን ለቀው ወጥተዋል።

መርማሪዎች ሚስማሮችን እና ሌሎች የብረት ቁርጥራጮችን እንዳገኙ አክለው፤ ፍንዳታው የተፈጠረው በተሻሻለ ፈንጂ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በትዊተር ገጻቸው ፍንዳታው የአሸባሪነት ተግባር መሆኑን ገልጸው አጥፊዎቹን ለመያዝ ቃል ገብተዋል።

"ሕዝቡ መፍራት የለበትም። ሌሎች ወንጀሎችን እንዳሸነፍነው ሁሉ ለሕይወት ክብር የሌላቸው አሳማዎች የፈጸሙትን ይህንን ወንጀልም እናሸንፋለን" ብለዋል።

እአአ በ2010 ካምፓላ ውስጥ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ሲመለከቱ በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች 74 ሰዎች ተገድለዋል። የኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል-ሸባብ አባላት የሆኑት የጥቃቶቹ አቀናባሪዎች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።