የሶማሊያው የፍቅር ፊልም ትልቁን የአፍሪካ የፊልም ሸልማት አሸነፈ

'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' የተሰኘው የሶማሊያ ፊልም

የፎቶው ባለመብት, BUFO FIMS

'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' [የመቃብር ቆፋሪው ሚስት] የተሰኘው የሶማሊያ ፊልም በፌስፓኮ የፊልም ፌስቲቫል አሸናፊ ሆነ።

በፊንላንዳዊ ሶማሊያዊው የፊልም አዘጋጅ ከድር አሕመድ የተሠራው ፊልሙ ከ16 ፊልሞች መካከል ነው አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው።

ፌስፓኮ ታዋቂ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ነው። ዘንድሮ ለ27ኛ ጊዜ በቡርኪና ፋሶ የተካሄደው ፌስቲቫሉ በአፍሪካውያን አፍሪካ ውስጥ የተሠሩ ፊልሞችን ያስተናግዳል።

ፊልሙ የሚያጠነጥነው ጉሌድ የተባለ መቃብር ቆፋሪ ላይ ነው። ሆስፒታል በር ላይ ሆኖ የሞቱ ሰዎች አስክሬን መጠባበቅ ዋናው ሥራው የሆነው ጉሌድ፤ ወደ መቃብር ቁፋሮ የገባው የታመመች ባለቤቱን ለማሳከም ነው።

የፌስፓኮ ፊልም ፌስቫል ዋና ዳኛ አብደራሕማን ሲሳኮ "ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚተርክ ቆንጆ ፊልም ነው" ብሎ ፊልሙን እንዳወደሰው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የፊልሙ አዘጋጅ አሕመድ በኢንስታግራም ገጹ ላይ "ደስታዬን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። ከአህጉረ አፍሪካ እንዲህ ያለ አድናቆት በማግኘቴ ምስጋናዬ የላቀ ነው" ብሏል።

በሶማሊያ ፊልም እምብዛም ባልተለመደ መልኩ ፊልሙ ዘለግ ያለ ፊቸር ፊልም ከመሆኑም በላይ በኦስካር ምርጥ ዓለም አቀፍ ፊልም ዝርዝር ውስጥ ለውድድር የቀረበ የመጀመሪያው የሶማሊያ ፊልም ነው።

መቼቱን ጂቡቲ ያደረገው ፊልሙ ጉሌድ የተባለው ዋና ገጸ ባህሪ የኩላሊት ታማሚ ባለቤቱን ለማሳከም ሲል የሚያልፈውን ውጣ ውረድ ያሳያል።

ጉሌድን ሆኖ የሚተውነው ኦማር አብዲ ሲሆን ባለቤቱ ናስራን ወክላ የምትተውነው ደግሞ ያስሚን ዋስሳሜ ናት።

አዘጋጁ ከጋርዲያግ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ "ፊልሙን በክብር እና በርህራሄ ለመሥራት ሞክሬያለሁ። እነዚህ ባህሪዎች የአስተዳደጌ አካል ናቸው" ብሏል።

ሶማሊያ የተወለደው አሕመድ ታዳጊ ሳለ ነው ወደ ፊንላንድ ያቀናው። ፊልሙን የጻፈው ከ10 ዓመት በፊት ቢሆንም እራሱ ፊልሙን ለማዘጋጀት ስለፈለገ ፊልም ሥራ እስከሚማር ድረስ 10 ዓመት ታግሷል።

ጎልደን ስታሊየን ኦፍ የኔጋ የተባለውን ሽልማት ከማግኘቱ በተጨማሪ 36,000 ዶላርም ተሸልሟል።

አሕመድ ያገኘው በወርቅ ደረጃ ያለውን ሽልማት ሲሆን፤ ከሱ በቀመጠል ያለውን የብር ሽልማት ያገኘችው 'ቴል ኦፍ ላቭ ኤንድ ዲዛየር' የተባለውን ፊልም የሠራችው ቱኒዝያዊቷ አዘጋጅ ለይላ ቦውዚድ ናት።