ለተሰንበት ግደይ የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰበረች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ ስፔን ቫሌንሺያ ዛሬ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበረች።
ቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን ትሪኒዳድ አልፎንሶ ኢዲፒ የተሰኘ ስያሜ በተሰጠው የዘንድሮው ውድድር ላይ የተሳተፈችው ለተሰንበት 1 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ52 በመግባት ነው ክብረ ወሰን የሰበረችው።
ባለፈው ዓመት የ5 ሺህ ክብረ ወሰንን በሰበረችበት መድረክ ላይ ነው ለተሰንበት ዛሬ በኬንያዊቷ አትሌት የተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ለማሻሻል የቻለችው።
ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲክ በያዝነው ዓመት ነበር የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰንን 1 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ02 ሰኮንድ መግባት የያዘችው።
የቶኪዮ ኦሊምፒክስ የነሐስ ባለቤቷ ለተሰንበት በዛሬው ውድድር ላይ የመጀመሪያውን 5 ኪሎ ሜትር በ15 ደቂቃ ነበር የሮጠችው።
ለተሰንበት የውድድሩን 10 ኪሎ ሜትር በ29 ደቂቃ ስታጠናቅቅ ይህም በግማሽ ማራቶን ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ለተሰንበት በአስደናቂ ፍጥነት ቀጣዩን 5 ኪሎ ሜትር በመሮጥ 15 ኪሎ ሜትር በ44 ደቂቃ 29 ሰኮንድ ማጠናቀቅ ችላለች።
ነገር ግን በመጨረሻው ሲሶ ፍጥነቷ በተነፃፃሪ ቢቀንስም በመጀመሪያዎቹ ኪሎ ሜትሮች ያስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት ክብረ ወሰኑን እንድትሰብር አስችሏታል።
በስተመጨረሻም 1 ሰዓት ከ02 ደቂቃ በ52 ሰኮንድ በመግባት በስሟ ሦስተኛውን ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች።
ለተሰንበት ግደይ በአሁኑ ወቅት የ10 ሺህ ሜትር፣ የ5 ሺህ ሜትርና ዛሬ ባስመዘገበችው ውጤት መሠረት ደግሞ የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ናት።
በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበረችው ሌላኛዋ ኢትዮጰያዊት የዓለምዘርፍ የኋላው ለተሰንበትን ተከትላ በ1 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ52 ሰኮንድ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።















