የቤይጂንግ ማራቶን በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋገረ

ቻይና ውስጥ በኮቪድ ሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና ውስጥ በኮቪድ ሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በመጨመሩ ምክንያት ቻይና የቤይጂንግ ማራቶን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ወሰነች።

ይህ የተወሰነው የአገሪቱ ዋነኛ የጤና ባለሥልጣን አዲስ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 1981 ጀምሮ በየዓመቱ የሚካሄደው የቤይጂንግ ማራቶን በቻይና ውስጥ የሚካሄድ ትልቁ የስፖርት ውድድር ነው።

ውድድሩ ሁሌም ቤይጂንን ከሚገኘው የታይናሚን አደባባይ ጀምሮ እዚያው ከተማ ውስጥ በሚገኘው የቤይጂንን ኦሊምፒክ ፓርክ ውስጥ የሚያበቃ ነው።

በመጪው እሁድ ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ በነበረው የቤይጂንግ ማራቶን ላይ 30,000 ሚደርሱ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

የቤይጂንግ ማራቶን አዘጋጆች ውድድሩን ለመሰረዝ የወሰኑት "የወረርሽኙን መስፋፋት በመቆጣጠር በሩጫው የሚሳተፉትን ስፖርተኞች፣ አስተባባሪዎችንና ነዋሪዎችን ጤናና ደኅንነትን ለመጠበቅ ነው" ብለዋል።

አስካሁን በቻይና ውስጥ ባሉ 11 ግዛቶች ውስጥ ተጨማሪ 133 በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ሁሉም በከፍተኛ ፍጥነት በሚተላለፈው ዴልታ በተባለው የቫይረስ አይነት መሆኑም ተነግሯል።

አሁን የተከሰተው የወረርሽኙ መስፋፋት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ናንጂን በተባለችው ግዛት ውስጥ ከተከሰተው ትልቁ ነው ተብሏል።

ይህ የወረርሽኙ ማንሰራራት ቻይና በሽታውን በመቆጣጠር በኩል ባላት ብቃት ላይ ጥያቄን ያስነሳ ሲሆን በተለይ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት በምታስተናገደው የክረምት ኦሊምፒክ ላይ ስጋት ፈጥሯል።

አሁን የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲስፋፋ ምክንያቱ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ግዛቶችና ከተሞች እየተዘዋወሩ ጉብኝት በሚያደርጉ የአገር ውስጥ የጉብኝት ቡድኖች አማካይነት እንደሆነ ተነግሯል።