የዝነኛው ቅርጫት ኳስ ተጨዋች ማይክል ጆርዳን ጫማ 1.47 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, SOTHEBY'S
አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ማይክል ጆርዳን አድርጎት የተጫወተበት ጥንድ ጫማ በጨረታ በ1.47 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠ ሲሆን ይህም ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ የተሸጠ የስፖርት ጫማ አድርጎታል።
ማይክል ጆርዳን ይህንን ጫማ እንደ አውሮፓውያኑ በ1984 ከቺካጎ ቡልስ ጋር በነበረው የመጀመሪያ ግጥሚያ ወቅት ተጫምቶት የነበረ ሲሆን ቀይ እና ነጭ ቀለም ያለው፣ የናይኪ ምርት የሆነና 'ኤር ሺፒንግ' የሚል ስያሜ ያለው ነው።
ያ ዓመት ማይክል የናይኪን የአልባሳት እና የጫማ ምርት ለመጠቀም ከኩባንያው ጋር የተፈራረመበት ወቅት ነበር።
ታዲያ ያ ጫማ አሁን ለጨረታ ቀርቦ የተሸጠበት ዋጋ በማንኛውም ስፖርት ከተሸጡ ጫማዎች ክብረ ወሰንን የሰበረ ነው ተብሏል።
በቅርጫት ኳስ ውድድር ውስጥ የገዘፈ ስም ያለው ማይክል፤ በ2003 ጡረታ የወጣ ሲሆን በአሜሪካ የቅርጫ ኳስ ሊግ ውስጥ የመጀመሪያው ቢሊየነርም ነው።
የጫማው በዚህ ዋጋ መሸጥ የማይክልን በቅርጫት ኳስ ውስጥ ያለውን ቦታ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ጫማውን በጨረታ አሸንፎ የገዛው ኒክ ፊዮሬላ የተባለ የተለያዩ ቁሶችን ገዝቶ በማሰባሰብ የሚታወቅ ሰው ነው።
ጨረታው ከመካሄዱ በፊት ጫማው ከ1 ሚሊዮን እስከ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሊሸጥ እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
ይህ ጫማ በስፓርቱ ዘርፍ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠ ጫማ ይሁን እንጂ ከስፓርት ውጪ ከዚህም በላቀ ዋጋ የተሸጡ ጫማዎች አሉ።
በዓለም በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው ጫማ የናይኪ 'ኤር ዬዚ 1' የተባለው የሙከራ ምርት (ፕሮቶታይፕ) ሲሆን፤ ራፐር ካንዬ ዌስት በ1.8 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶታል።












