ከኢትዮጵያ ያመለጠው ኤርትራዊ ሰው አዘዋዋሪ በኔዘርላንድስ በጥብቅ ከሚፈለጉ ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

ሰደተኞች በጀልባ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ኤርትራዊውን በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት የሚፈለገውን ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያምን በሕግ በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካተተ።

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያም ከሚቀርቡበት በርካታ ክሶች መካከል ግድያ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም የሚሉት ይገኙበታል።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ኤርትራዊው ተይዞ በወንጀል እንዲጠየቅ በሚል በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳካተተው ተዘግቧል።

ኪዳኔ በአዲስ አበባ ለአንድ ዓመት ገደማ የሁለት ስደተኞች ግድያን ጨምሮ በስምንት ሰዎች ዝውውር ተከሶ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ሳለ ማምለጡ ይነገራል።

በፍርድ ቤት ቀጠሮ ዕለት ከፍርድ ቤት ማምለጡ በርካቶችን ያነጋገረ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለፍርድ እንዲቀርብ ንቅናቄ የሚያደርጉ የመብት ተሟጋቾችን ያስቆጣ ነበር።

ትውልደ ኤርትራውያን የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ብዙ የሌሎችም አገራት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ግለሰቡ ለፍርድ እንዲቀርብ በተለያየ ጊዜያት ጥሪ አቅርበዋል።

ኪዳኔ ከእስር ቢያመልጥም ፍርድ ቤቱ በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶበታል። አሁን የት እንዳለም በትክክል አይታወቅም።

ግለሰቡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሊቢያ ውስጥ የሚጠባበቁ አፍሪካውያን ስደተኞችን በማስራብ፣ በማሰቃየት እና በማንገላታት ክሶች ነው።

ኪዳኔ አዲስ አበባ ውስጥ ከወራት በፊት የፍርድ ሂደቱ እየታየ ነበር ከፍርድ ቤት እንዳመለጠ የተዘገበው። በእሱ እንግልት ከደረሰባቸው ግለሰቦች አንዱ ባደረጉት ጥቆማ ነበር በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው።

በወቅቱ "መጸዳጃ ቤት ውስጥ ልብስ ቀይሮ" ከፖሊስ እጅ እንዳመለጠ መዘገቡ አይዘነጋም።

በኪዳኔ ስም ገንዘብ በመቀበል አብራው የተከሰሰችው ሳባ መንድር ኃይሌ የ12 ዓመት እስር ተፈርዶባታል። ሌላው የእሱ ተባባሪ እንደሆነ የሚነገረው እና ዋሊድ በሚል ስም የሚታወቀው ተወልደ ጎይቶም በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው፤ እአአ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ኪዳኔ እና ተወልደ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሊቢያ ውስጥ አዘዋውረዋል።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ከጣልያን ጋር በመተባበር ኪዳኔን ይዞ ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ እንዳለው፤ ኪዳኔ ወደ ኔዘርላንድስ መሄድ የሚፈልጉ ኤርትራውያንን በመድፈር፣ በማሰቃየት፣ በማገት እና ገንዘብ በመንጠቅ ወንጀሎች ተጠያቂ እንደሆነ የምርመራ ውጤታቸው ያሳያል።

ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስ እና ኔዘርላንድስ ውስጥ የሚኖሩ የስደተኞች ቤተሰቦች ገንዘብ እንዲልኩ እንደሚገደዱ ተገልጿል።

በደች ሕግ መሠረት ኔዘርላንድስ ውስጥ የሚኖር ሰው ላይ ጉዳት ያደረሱ የሌሎች አገራት ዜጎች ለፍርድ የሚቀርቡበት አሠራር አለ። ይህም ከዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ የሕግ ተጠያቂነት ጋር የሚገናኝ ነው።

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያም ማነው?

ኪዳኔ "የዓለማችን እጅግ አደገኛ እና ጨካኝ ሰው አዘዋዋሪ" በሚል በተደጋጋሚ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይገለጻል።

ሊቢያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የሚገኙበት ካምፕ እንዳለውም ይነገራል።

ከስደተኞች እንዲሁም በሌሎች አገራት ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በግዳጅ ገንዘብ በመቀበል የሚታወቅ የወንጀል ቡድን መሪ እንደሆነም ይከሰሳል።

ይህ ቡድን ስደተኞችን በመድፈር፣ በማገት፣ በመደብደብ እና አጠቃላይ ሰብአዊ መብታቸውን በመግፈፍ በተፈጸሙ በደሎች በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

በኪዳኔ እንደሚመራ የሚገለጸው የወንጀል ቡድን ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሊቢያ የሚጠባበቁ ስደተኞችን በማፈን በአውሮፓ ወይም በሌላ አገር ካሉ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመቀበል ይወነጀላል።

ሊቢያ ውስጥ ባለው ባኒ ዋሊድ በሚባል ከተማ ውስጥ ይገኛል በተባለው ካምፕ ውስጥ ስደተኞች ከአንድ ዓመት በላይ ይታገታሉ።

ካምፑ ውስጥ ስደተኞች ከገቡ በኋላ ከሱዳን ወደ አውሮፓ አገራት ለመጓዝ እንከፍላለን ብለው ከተስማሙት ገንዘብ በላይ ይጠየቃሉ። እነሱ ወይም ቤተሰቦቻቸው ገንዘቡን እስኪከፍሉም ስቃይ ይደርስባቸዋል።

ይህ ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚሉት፤ የሚጠየቁት ገንዘብ ከ5,000 ዶላር እስከ 12,000 ዶላር ይደርሳል።

የስደተኖች ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ንቅናቄ በማድረግ የሚታወቁ የመብት ተሟጋቾች፤ ኪዳኔ "በርካታ ስደተኞች ላይ ላደረሰው በደል በሕግ እንዲጠየቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መረባረብ አለበት" ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ሰዎች ሊቢያ ውስጥ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል። በሊቢያ ያለውን አለመረጋጋት ተጠቅመው ስደተኞቹን የሚያሰቃዩ፣ የሚበዘብዙ፣ ገንዘብ የሚነጥቁና ገፋ ሲልም የሚገድሉ ሰው አዘዋዋሪዎች ጉዳይም አሳሳቢ ሆኗል።

ኪዳኔ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የወንጀል ምርመራ የሚፈለግ ሰው እንደሆነ የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው፤ የ37 ዓመቱን ኪዳኔ በቁጥጥር ስር ለማዋል የኔዘርላንድ መንግሥት ከተለያዩ አገራት ጋር እንደሚሠራ አስታውቋል።

"በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ እንዲዘዋወሩ እና እጅግ በሚያዋርድ ሁኔታ እንዲገላቱ ምክንያት የሆነው ሰው ለፍርድ መቅረብ አለበት" ሲልም የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ አውጥቷል።