ሰሜን ኮሪያ ከሰርጓጅ መርከብ የሚተኮስ ባሊስቲክ ሚሳኤል ሞከረች

ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, KCNA VIA REUTERS

ሰሜን ኮሪያ ማክሰኞ ዕለት ከሰርጓጅ መርከብ የሚተኮስ ባሊስቲክ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ይፋ አደረገች።

በመንግስት የሚተዳደረው የመረጃ አውታር 'ኬሲኤንኤ' እጅግ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሚሳኤል ሌሎች እንዳይከታተሉት ተደርጎ የተሰራ ስለመሆኑ ዘግቧል።

ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ሳምንታት እጅግ ፈጣን የሆኑ ሃይፐርሶኒክ እና ረጅም ርቀት ተጓዥ የሆኑ ናቸው የምትላቸውን ሚሳኤሎች እና ጸረ ከባድ መሳሪያዎችን መሞከርን ተያይዛለች።

የተባበሩት መንግስታት ደግሞ የባሊስቲክ ሚሳኤል እና የኒኩሌር መሳሪያዎችን ሙከራ አግዷል።

ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ከክሩዝ ሚሳኤል የበለጠ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎች ናቸው። ምክንያቱም ደግሞ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ክብደት የመሸከም አቅማቸው ከፍተኛ ሲሆን በፍጥነት የመጓዝና ረጅም ርቀት የማካለል አቅምም አላቸው።

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዕለት እንደዘገቡት ከሆነ የተሞከረው አዲሱ ባሊስቲክ ሚሳኤል የተገጠመለት ዘመናዊ መቆጣጠሪያ መሳሪያ በጎንዮሽ እንዲምዘገዘግ ረድቶታል።

ትናንት የተተኮሰው ባሊስቲክ ሚሳኤል ፒዮንግያንግ ባለፈው ሳምንት አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿን ባሳየችበት ኤግዚቢሽን ላይ ለእይታ ቀርቦ ነበር።

ስለሙከራው በወጡ ዘገባዎች ላይ የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ስም አልተጠቀሰም። በዚህም በሙከራው ስነ-ስርዓት ላይ እንዳልተገኙ ተገምቷል።

ማክሰኞ ዕለት የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች እንደገለጹት በምስራቃዊ ሰሜን ኮሪያ ከምትገኘው ሲንፖ ደሴት አቅራቢያ ሚሳኤል የተተኮሰ ሲሆን አካባቢውም ሰሜን ኮሪያ ሰርጓጅ መርከቦቿን በማዕከልነት የምትመራበት ቦታ ነው።

ሚሳኤሉም ኢስት ባህር ወይም የጃፓን ባህር ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል ላይ አርፏል። የሚሳኤሉ ፍጥነትም በሰዓት 450 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር። ከምድር ደግሞ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲምዘገዘግ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዎቿን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን ደቡብ ኮሪያም ቢሆን የራሷን ረቂቅ መሳሪያዎች እያበለጸገች ነው። የአካባቢው ተንታኞችም ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ፉክክር ውስጥ ስለመግባታቸው እየገለጹ ነው።

ሴዉል በቅርቡ ከሰርጓጅ መርከብ የሚተኮስ እጅግ ዘመናዊ ሚሳኤል ይፋ ያደረገች ሲሆን ይህም አገሪቱ ካደረገቻቸው ወታደራዊ ትዕይንቶች ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል። በቅርቡም ደቡብ ኮሪያ የራሷን ሮኬት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች።

ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በኮሪያ ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ በኋላ ሁለቱ አገራት በጦርነት ጫፍ ላይ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ቆይተዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ሳምንት ጦርነቱ በድጋሚ ቢቀሰቀስ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው ነበር።

የሰሜን ከሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ሳምንት በኮሪያ ባህረሰጤ በድጋሚ ጦርነት እንዲቀሰቀስ እንደማይፈልጉ ገልጸው ነበር። ነገር ግን አገራቸው እራሷን አሜሪካን ከመሰሉ ጠላቶች ለመከላከል ስትል ከባድ መሳሪያዎችን እያበለጸገች እንደሆነ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊዎች በደቡብ ኮሪያ መዲና ስለ ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ እና የኒውክለር ማብለያዎች ውይይት እያደረጉ ነው።

አሜሪካ የተጣሉት ማዕቀቦች ከመነሳታቸው በፊት ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያዎቿን ታስወግድ የምትል ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በዚህ ሃሳብ በጭራሽ አልስማማም ብላ ቆይታለች።