ከባቄላ እና ገብስ ለሕፃናት አልሚ ብስኩት ያዘጋጁት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, NAOL
አራት ናቸው። አራቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ እና በአንድ ዶርም ውስጥ የሚኖሩ።
ጓደኛሞቹ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት "ማሕበረሰባችንን እንዴት እናግዝ?" የሚል ጥያቄ አንስተው ብዙ መከሩ፣ ሐሳብ ተለዋወጡ አልፎም ተጨቃጨቁ።
ከዚያም አንድ ሐሳብ ላይ ደረሱ። ባቄላ እና ገብስ በመጠቀም ለኢትዮጵያውያን ሕፃናት የሚሆን አልሚ ብስኩት ማበልጸግ እና ማምረት።
ወጣቶቹ ለዚህ ሐሳብ መነሻ የሆናቸው በርካታ ሕፃናት ለፕሮቲን እጥረት በመጋለጣችው ምክንያት ለመቀንጨር እና ለሌሎች ችግሮችም መዳረጋቸውን ማስተዋላቸው እንደሆነ አልሚ ምግቡን ካበለጸጉ አንዱ የሆነው ናኦል አዱኛ ይገለጻል።
በፕሮቲን እጥረት ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ሕይወታቸው ያልፋል። ታዲያ ይህ እውነታ ተማሪዎቹ እሩቅ መጓዝ ሳይጠበቅባቸው ባቄላ እና ገብስ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።
እንደ ናኦል እና ጓደኞቹ ምልክታ፤ በኢትዮጵያ ሰዎች ገብስ እና ባቄላን የሚመገቡበት መንገድ ከንጥረ ነገሮቹ የሚመነጨውን ጥቅም በደንብ ለማግኘት የሚያግዝ አይደልም።
"ገብስ እና ባቄላን ሕዝባችን ሲጠቀምበት የነበረው መንገድ ንጠረ ነገሮቹን በደንብ እንድንጠቀምበት ተደርጎ አይደለም። እኛ ደግሞ እነዚህን ሁለት ነገሮችን ወስደን ብስኩት ሠራን" የሚለው ናኦል፤ "በአገራችን ውስጥ ሕፃናት ላይ የፕሮቲን እጥረት፣ የመቀንጨር እና እንደዚህ አይነት ችግሮች ይታያሉ። እናም ትልቁ አላማችን ይህንን ችግር መፍታት ነው" ሲል ያስረዳል።
ከዚህም ባሻገር የአልሚ ምግቦች ዋጋ ውድ የሚባል እንደሆን በመጠቀስ 'ፋባርሊ' የሚል ስያሜ የሰጡትን ብስኩት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ሌላኛው አላማቸው ነው።
![ይህ በኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች የበለጸገው አልሚ ምግብ አሁን ላይ የሙከራ ምርት [prototype] ደርጃ ላይ](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/5279/production/_121131112_whatsappimage2021-10-15at18.24.11.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, NAOL
ይህ በኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች የበለጸገው አልሚ ምግብ አሁን ላይ የሙከራ ምርት [prototype] ደርጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው አሸናፊ ሆነዋል። ወደ ዴንማርክ በማቅናትም ምርታቸውን በቤተ ሙከራ ለማሳየት በቅተዋል።
የዚህ ሐሳብ መነሻ ምንድን ነው?
ናኦል የተወለደው ከሜሴ ነው። በተለይም በገጠራማው ክፍል ድርቅ እና ረሃብ የሚከሰትበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል።
"ሕፃን እያለሁ እንደዚህ አይነት ችግሮች ያጋጥሙ ነበር። የተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡት ብስኩት ነበርና እነዛን ብስኩቶች ስንበላ ምን ያህል ደስ እንደሚለን ትዝ ይለኛል። እናም እነዛን ብስኩቶች እንዴት አድርገን እናግኝ ብዬ አስብ ነበር" ይላል ናአል።
ናኦል ይህንን የልጅነት ትውስታውን ለጓደኞቹ ኪሩቤል እንግዳወርቅ፣ ሙሴ አብርሃም እና ዮሴፍ ታሪኩ ካጋራ በኋላ ነበር ፋባርሊ ብስኩት የተጠነሰሰው።
ብስኩቱን ለማበልጸግ በርካታ ጥናቶችን እንዳደረጉ የሚጠቅሰው ናኦድ፤ ከዓለም የምግብ ፕርግራም እና ዴንማርክ ውስጥ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግሯል።
የፋርማሲ ተማሪዎች መሆናቸው እና ቤተ ሙከራ ውስጥ ረዘም ያለ ሰዓት ማሰላፋቸው ይህንን ሐሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር ምቹ እድል እንደፈጠረላቸው ያስረዳል።
"ይህ ፕሮጀክት ከእኔ ሕይወት ብዙ የቀሰመው ነገር አለ። የመማር ፋላጎት ያላቸው ሕፃናት ትምህርቱን ወደው እንዲማሩ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ጠግበው እና አዕምሯቸው ፋፍቶ መሆን አለበት። ልጆች የማሰብ አቅማቸው አድጎ ማሰብ ባለባቸው ደረጃ ማሰብም ይገባቸዋል። ለዚህ ነው ሕፃናትን ለመርዳት እና ለማሳደግ የተነሳነው።"
በኢትዮጰያ በስፋት ከሚበቅሉት ባቄላ እና ገብስ የሚመረው ይህ አልሚ ብስኩት ለሕፃናት በሚመች መልኩ የሚቀርብ ነው።
በርካታ የአልሚ ምግብ አይነቶች በፈሳሽ እና በብስኩት ቅርጽ ይመረታሉ፤ ታዲያ የእናንተ አልሚ ምግብ ከእነዚህ በምን ይለያል? የሚል ጥያቄ ያቀርብንለት ናኦል - ብስኩቱ እስከዛሬ ባቄላ እና ገብስ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በመቀየር ከንጥረ ነገሮቹ የሚገኘውን ጥቅም በሚገባ ለመጠቀም ያስችላል ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት
ጤናማ እና ለሕፃናት ተስማሚ የሆነ ምግብ በዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብ የወጣቶቹ ዋነኛ ግብ ሲሆን፤ የጥራት ማረጋገጫ ማግኘትን ጨምሮ የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ በስፋት ለማምረት እና ለገበያ ለማቅረብ እየጣሩ ነው።
ወደ ዴንማርክ ባቀኑበት ወቅት ያገኙትን አበል፣ በሽልማት እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ያገኙትን ገንዘብ በማሰባሰብ በ150 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ብስኩቱን ለገበያ ለማቅረብ ወጣቶቹ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
"[150 ሺህ ብሩ] ቤት ለመከራየት፣ የተወሰኑ ቁሳቁሶችን ለሟሟላት ይጠቅመናል ብለን እናስባለን። አላማችን ትልቅ ቢሆንም በአንድ ጊዜ ትልቅ መሆን አንችልም። ካለችን ነገር ነው ትንሽ ነገር ለማድረግ እየሞከርን ያለነው። እውነት ለመናገር አሁን ያለን ካፒታል በጣም ትንሽ ናት። በእርግጠኝነት በጣም ብዙ ታፈራለች ብለን እናምናለን" ይላል ናኦል።

የፎቶው ባለመብት, NAOL
ጨምሮም "ይሄ ለሌሎች ትምህርት ይሆናል ብለን እናስባለን። እንደዚህ አይነት ነገር የሚሞክሩ ሰዎች ከሚሊዮን መጀመር አይጠበቅባቸውም። አካባቢያቸው ላይ ባለ ነገር ማሕበረሳበቸው ላይ መልካም ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላሉ ብለን እናምናለንም" ሲል ተናግሯል።
ምግቡ በስፋት ሲመረት 100 ግራም ብስኩት በ10 ብር ለመሸጥ ያቀዱ ሲሆን፤ የምጣኔ ሀብት ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ የዋጋ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ሳይጠቅስ አላለፈም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ሳቢያ በርካታ ሕፃናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደተጋለጡ እና የረሃብ ስጋት እንደተጋረጠባቸውም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገልጸዋል።
ናኦል አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተኑ ለሚገኙ ሕፃናት የዚህ አይነት ፕሮጀክቶችን አስፈላጊነት ሲያስረዳ- "አብዛኛው ልጆች ከትምህርት ገበታ የተፈናቀሉበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ይሄ ደግሞ ለተለያየ ችግር እንደሚያጋልጣቸው የታወቀ ነው። ይሄ ፕሮጀክት ትልቅ አቅም አለው። እነዚህ ልጆች አሁን ላይ ጥሩ የሆነ እድገት እንዲኖራቸው ጥሩ የሆነ አቅርቦት ማግኘት አለባቸው።"
ናኦል እና ሦስቱ ጓደኞቹ ይህንን ብስኩት በስፋት በኢትዮጵያ ለማዳረስ እና ሕፃናትን ለመርዳት ወደፊት ከትምህርት ተቋማት ጋር የመሥራት እቅድ አላቸው።












