በኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መጋለጣቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, OCHA
በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በምስራቃዊ ኬንያ፣ በደቡባዊ ሶማሊያ እና የበልግ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅት ከሚጠበቀው በታች የዝናብ መጠን በመገኘቱ የምግብ ዋስትና ችግር መከሰቱን መሆናቸው የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) አስታወቀ።
ኦቻ በአከባቢዎቹ ከአማካይ በታች የሰብል ምርት፣ የግጦሽ መሬት መመናመን እና በአከባቢዎቹ ላይ የእህል ዋጋ መጨመር መከሰቱን አስታቋል።
እንደ አውሮፓውያኑ ከመስከረም 2021 ጀምሮ በኢትዮጵያ 401 ሺህ 313 ሰዎች እንዲሁም በደቡብ ሱዳን 108 ሺህ ለአስከፊ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ ሰዎችን ጨምሮ በኢጋድ ውስጥ በሚጠቃለሉ አገራት ከ29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ገጥሟቸዋል።
በተጨማሪም 8.3 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ የምግብ እጥረት አጋጥሞቸዋል። እአአ 2020 በኢጋድ ቀጠና ውስጥ ለ3.5 ሚሊዮን ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት አስቸኳይ የተመጠጠነ ምግብ አቅርቦት የቀረበ ሲሆን አሁን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ እንደሚል ኦቻ አስታውቋል።
ግጭት፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ተፅህኖ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች በተከታታይ ከተከሰተው የዝንናብ እጥረት ባሻገር የምግብ ዋስትና ችግር እንዲባባስ በምክንያትነት ተቀምጠዋል።
እንደተለያዩ ዓለም አቀፍ ትንበያዎች ከሆነ በጥቅምት እና ታህሳስ መካከል በሚጠበቀው የዝናብ ወቅት በድጋሚ ከአማካይ በታች ዝናብ የመከሰተ እድል ያለ ሲሆን በአየር ሁኔታዎች ውስጥ ምንም ዋና መሻሻሎች አይታዩም።
በሌላ በኩል የአጭር ጊዜ ትንበያዎች እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ አንዳንድ ክፍሎች ላይ ከሚጠበቀው በተቃራኒ የዝናቡ ወቅት መጀመሩን ያሳያሉ ይላል ኦቻ።
በተጨማሪም በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ በመጋቢት፣ ሚያዚያ እና ግንቦት ወራት ላይ ከአማካይ በታች የዝናብ ሁኔታ የመከሰት ዕድሎች መኖራቸውን ያመለክታሉ።
እንደ ትንበያዎች ሌላ ዝቅተኛ የዝናብ ወቅት መከሰት ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የምግብ ዋስትና ችግሮችን እንደሚያባብስም አመላክቷል።
ቀደም ሲል በቂ የመኸር ወቅቶች ሰብሎች ላላገኙ አርሶ አደሮች መጪው የዝናብ ጊዜ ከተጠበቀው በታች መሆን የምግብ ክምችት ከተለመደው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲሟጠጥ እና ቤተሰቦች ሽመታ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል ያለው ኦቻ፤ ለአርብቶ አደሩ ደግሞ ውስን የግጦሽ እና የውሃ አቅርቦት እንዲኖረው በማድረግ እንስሳቱ ደካማ የሰውነት ሁኔታ እንዲኖራቸው፣ ዋጋቸው ዝቅ እንዲል እና የወተት ምርት እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሷል።
ኦቻ አፋጣኝ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ የምግብ ዋስትና እጠረቱ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና የሶማሊያ አከባቢዎች የምግብ ዋስትና ችግሩና እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ መጠን እያደገ መምጣቱ እንደማይቀር ድርጅቱ አሳስቧል።
እአአ በ2011 እና 2017 አከባቢው በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ማለፉን ያስታወሰው ኦቻ በተለይ በሶማሊያ ርሃብ እንዲከሰት ጭምር አድርጓል ብሏል።












