ተመድ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሁለተኛዋን የኢትዮጵያ ኃላፊ ጠራ

የፎቶው ባለመብት, UNFPA Ghana
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያልተገባ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለተኛዋን የተመድ የኢትዮጵያ ኃላፊን ጠራ።
የተመድ ሥነ ሕዝብ ጽህፈት ቤት (ዩኤንኤፍፒኤ) የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል መጠራታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ማከሰኞ ምሽት ዘግቧል።
ቀደም ሲል የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን አቻንግ "የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ" አስተያየት በመስጠታቸው ምክንያት አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን ተቋሙ ለቢቢሲ አስታውቆ ነበር።
መንግሥታቱ ድርጅት የሥነ ሕዝብ እና የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊዎች ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገናል ስለማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሁለቱ በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ ኃላፊዎች የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ በተመለከተ በርካታ መጣጥፎችን ለሚፅፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።
በቃለ መጠይቁ ላይ እንደሚሰማው የአይኦኤም ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ብለዋል።
ህወሓትንም "ቆሻሻ" እና "ጨካኝ" በማለትም ሲናገሩም ይሰማል።
በአንድ ወቅትም ህወሓት ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ የትግራይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ አሲረዋል በማለትም ሲከሱ ይሰማል።

የሥነ ሕዝብ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ጌይል ደግሞ ኢትዮጵያ የገቡ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች አዲስ አበባ የሚገኙ ከፍተኛ የተመድ ኃላፊዎችን በማለፍ በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ ይላሉ። ይህም የሚያመለክተው "በተመድ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ" ስለመኖሩ ሲሉ ጌይል ይሰማሉ።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ የሥነ ሕዝብ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል እና የስደተኖች ጉዳይ ድርጅት ኃላፊዋ ወደ ኒው ዮርክ መጠራታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚደረገውን ሥራ የበለጠ እንደሚያውከው ተጠቅሷል።
ተመድ በኢትዮጵያ የአይኦኤም ኃላፊን በጠራበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም አመላክተው ነበር።
ቢልለኔ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ "የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ከሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው ማውሪን አቺየንግ ላይ የተጣለው አስተደዳራዊ እረፍት በጣም የሚረብሽ ነው" ብለው ነበር።
አክለውም "በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያለው ውስጣዊ እና የውጭ ተፅእኖ ፓለቲካ በጥልቀት መመርመር እንዳለበት" በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ በወገንተኝነትና እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ደቅነዋል ያለቻቸውን የተመድ ሰባት ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።












