ፈጠራ፡ በቆሎን ወደ ቢራ የቀየረው የዩኒቨርስቲ ተማሪ

"ከበቆሎ ቢራና ውስኪ ማምረት ችያለሁ።" ይህንን የሚለው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአራተኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ኤርሚያስ ዋቅሹማ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም ውስኪን ለማምረት ይወስድ የነበረውን ከ7 እስከ 10 ዓመት ጊዜ፣ ኤርሚያስ በማሳጠር በሶስት ወር ውስጥ ማምረት መቻሉን ይናገራል።
ይህ የምርት ጊዜውን አሳጥሮ ተፈላጊ ምርት ማግኘት መቻል የእርሱ የፈጠራ ሃሳብ እና ውጤት መሆኑን አክሎ ያስረዳል።
ኤርሚያስ በቆሎን ተጠቅሞ ቢራና ውስኪ ማምረት የፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዳ የተትረፈረፈ ምርት በአገሪቱ ውስጥ መኖሩን በማንሳት ነው።
ቢራ በተለምዶ ከገብስ እንደሚመረት የሚናገረው ኤርሚያስ ባለፉት ስድስት ወራት በቆሎ ላይ አተኩሮ በመስራት ጥሩ የሚባል የአልኮል መጠጥ ምርት ማግኘቱን ይናገራል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በቆሎ በስፋት እንደሚመረት የሚናገረው ኤርሚያስ ለዚህ የፈጠራ ሃሳቡም ይህ መነሻ ሆኖ አገልግሎታል።
ኤርሚያስ በቆሎ በመላው አገሪቷ ክፍሎች መመረት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የምርት መጠን ያለ መሆኑንም አስተውሏል።
ይህ የእህል ዘር ከሌሎች ምርቶች በተለየ ለገበያ የሚቀርበው በዝቅተኛ ዋጋ መሆኑን ጨምሮ የሚናገረው ኤርሚያስ ዋቅሹማ፣ ይህ በቀላሉ ለኢንዱስትሪው ግብዓት ቢሆን በአነስተኛ ዋጋ ምርትን ለማቅረብ እንደሚያስችል ይናገራል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተማሪው ኤርሚያስ፣ ቢራ ለማምረት የፈለገበት ሌላ ምክንያት በአሁን ሰዓት ይህ የአልኮል መጠጥ ያለውን የደንበኞች ብዛት በማስተዋል ነው።
ይህ ከፍተኛ የደንበኛ ቁጥር እያገኘ ያለ ኢንዱስትሪ በእንደዚህ ዓይነት ፈጠራ ቢታገዝ የምርት ጥራቱ ሳይወርድ በዝቅተኛ ዋጋ የደንበኞቹን ፍላጎት ማርካት እንደሚችል ይናገራል።
በተጨማሪም የቢራ አምራች ፋብሪካዎች የተወሰኑ ምርቶቻቸውን ከባህር ማዶ በውጭ ምንዛሬ ተጠቅመው እንሚያስገቡ ያስተዋለው ኤርሚያስ፣ እርሱ በፈጠራ ስራዎቹ ይህንን ለማስቀረት ቢሰራ ኢትዮጵያ የተወሰነ የዶላር ወጪዋን እንደምታድን አስልቷል።
ወደ ኢትዮጵያ ውስኪ የሚገባው ከባህር ማዶ መሆኑን የሚናገረው ኤርሚያስ አገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምዛሬ ማዳን ወደ ባህር ማዶ በመላክ ደግሞ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ይናገራል።
ይህንን ሃሳቡን በቅድሚያ ለሚማርበት ዩኒቨርስቲ በፕሮፖዛል መልክ አቅርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ ወደ ምርመር ስራው መግባቱን ኤርሚያስ ያስታውሳል።
ባለፉት ስድስት ወራት በዚህ ስራ ላይ በተሰማራበት ወቅት ውጣ ውረዶች እንደነበሩ የሚያስረዳው ኤርሚያስ፣ ሁሉንም በድል ለመወጣት ከአንቅልፍ ተፋቶ፣ ጊዜውን ሰውቶ መስራቱን ያስረዳል።
ከተግዳሮቶቹ መካከል በቂ የገንዘብ ድጋፍ አለመኖር፣ የሚሰራውን ስራ ለሌሎች አስረድቶ ወይንም አቅርቦ ተቀባይነት የማግኘት ችግር ነበረበት።
የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው ኤርሚያስ ሌላው የነበረበት ተግዳሮት ትምህቱን ከምርምር ሰዓቱ ጋር አጣጥሞ መሄድ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከትምህርት ሰዓት ውጪ፣ ሊሊት ጭምር በቤተ ሙከራ ውስጥ ማሳለፍ ይጠይቀው እንደነበር የሚናገረው ኤርሚያስ፣ ነገር ግን በጽናት በውጤት ማጠናቀቁን ይናገራል።

ኤርሚያስ በአሁን ሰዓት በሙከራ ደረጃ፣ ከሄኒከን ቢራ ጋር በመተባበር 100 ሊትር ቢራ አምርቷል።
ባለፈው ወር የኢንዱስትሪው ተወካዮች እንዲሁም የዩኒቨርስቲው አስተዳደር እና መምህራን በተገኙበት የቅምሻ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በጎ ምላሽ እንዳገኘም ያስረዳል።
ኤርሚያስ ይህንን አዲስ የምርምር ውጤት መስራት የጀመረው በኮቪድ-19 ወቅት ሲሆን፣ የሚማርበት ዩኒቨርሲቲ እና ሄኒከን ቢራ ፋብሪካ ለስራው ስኬት ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል።
ይህ የቢራ ምርት ገበያ ላያ ወጥቶ ገበያ ላያ ካሉት ሌሎች ምርቶች ጋር ተፎካክሮ ሲሸጥ የማየት ህልም አለው።
በእርሱ እጅ የተመረተ ቢራ በሁሉም የቢራ አፍቃሪያን እጅ ቢገኝ በሁሉም የቢራ አፍቃሪያን ጉሮሮ ቢንቆረቆር ደስታው ነው።
ኤርሚያስ ያመረተው ቢራ የአልኮል መጠኑ 4.79% ነው። ይህም ገበያ ላይ ካለው ቢራ ጋር የሚወዳደር መሆኑን ገልጿል።
እንዲሁም "የጠመቅኩት ውስኪ አልኮል መጠኑ 42 % ነው። ይሄም ቢሆን ገበያ ላይ ከሚገኘው ውስኪ ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው ነው" ሲል በኩራት ይናገራል።
አብረው የሚሰሩት አጋሮች እንደሚፈልግ የሚናገረው ኤርሚያስ፣ በቀጣይ ዓመታት ወደ ገበያ ይገባል የሚል እምነት አለው።
ኤርሚያስ ዋቅሹማ፣ የፈጠራ ሥራውን በአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ለማስመዝገብ እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

















