እስራኤል እንደ አይሁድ እንድትቀበላቸው የሚፈልጉት ናይጄሪያውያን

የፎቶው ባለመብት, Irums
ሽሎሞ ቤን ያኮቭ በናይጄሪያ ዋና ከተማ በአቡጃ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ምኩራብ ወደ ኋላ እና ወደ ፊት እየተወዛወዘ ከቶራህ ጥቅል መካከል ያነብባል።
አልፎ አልፎ ለስላሳ ድምፁ በዕብራይስጥ ከፍ ይል እና ከእሱ በኋላ በሚያነቡት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ይቀላቀሉታል።
አብዛኛዎቹ ቋንቋውን ሙሉ በሙሉ አይረዱትም። ሆኖም የዚህ ትንሽ የናይጄሪያ ማህበረሰብ የዘር ሃረግ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ከአይሁድ እንደሚመዘዝ ይናገራሉ። በእስራኤል ዕውቅና ባለማግኘታቸው ግን ተስፋ ቆርጠዋል።
ያኮቭ "ራሴን እንደ አይሁድ እቆጥረዋለሁ" ይላል።
በጂክዎይ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የግዮን የዕብራይስጥ ምኩራብ ሱኮትን ለማክበር ከዘንባባ ቅጠሎች በተሠራ ድንኳን ውስጥ አንድ ጠረጴዛ ተቀምጧል። ሱኮት አይሁዶች ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ በረሃ ላይ ያሳለፉትን ዓመታት የሚያስታውስ በዓል ነው።
ሰዎች ባህላዊ የቾላ ዳቦ (በምኩራቡ የተጋገረ ዳቦ ነው) እና ከትንሽ ኩባያዎች የወይን ጠጅ በመቀባበል ይቋደሳሉ። "እኛ አሁን እንደምናደርገው በእስራኤል ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ" ይላል ያኮቭ።
እሱ ኢግቦ ነው። ኢግቦ ከሀገሪቱ ሦስት ታላላቅ ጎሳዎች አንዱ ሲሆን መነሻውም ከደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ነው። የኢግቦ ስሙም ንናሜዙ ማዱዋኮ ነው።
ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ያኮቸቭ የአይሁድ እምነትን ባይከተሉም የአይሁድ ዘር ሐረግ እንዳላቸው እና ብዙ ኢግቦዎች ከጠፉት 10 የእስራኤል ነገዶች አንዱ እንደሆኑ ያምናሉ። እነዚህም ከ 35 ሚሊዮን ኢግቦዎች ከ 0.1 በመቶ በታች ናቸው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 8ኛው ክፍለ ዘመን የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ድል በተደረገበት ጊዜ እነዚህ ጎሳዎች ወደ ምርኮ በግዞት ከተወሰዱ በኋላ ጠፍተዋል ተብሏል። ለምሳሌም የኢትዮጵያ አይሁድ ማህበረሰብ እንደ አንዱ ሆኖ ዕውቅና ተሰጥቶታል።
የኢቦብ ልማዶች የሆኑት እንደ ወንድ ልጅ ግርዛት፣ የሞቱ ሰዎችን ለሰባት ቀናት በሃዘን ማሰብ፣ አዲስ ጨረቃን ማክበር እና በሰገነት ስር የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን ማካሄዳቸው ስለአይሁድ የዘር ሐረግ ያላቸውን እምነት ያጠናክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Irums
'ማስረጃ የለም'
በኢኑጉ በሚገኘው በናይጄሪያ ዩኒቨርስቲ አንትሮፖሎጂስት የሆኑት ኢግቦው ቺዲ ኡግዉ ይህ የይሁዲነት ማንነት ብቅ ያለው ከቢያፍራ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ነው ይላሉ።
ኢግቦዎቹ ከናይጄሪያ ለመገንጠል ይታገሉ ነበር። ከ 1967 እስከ 1970 ባለው ጊዜ በተካሄደው ከባድ ግጭት ተሸንፈዋል።
አንዳንድ ሰዎች "የሚንጠለጠሉበት አንዳንድ የስነልቦና ማበረታቻን ይፈልጉ ነበር" ስለሆነም የአይሁድን ግንኙነት መፈለግ ጀመሩ።
አይሁዶች በታሪክ በተለይም በጅምላ ጭፍጨፋ ወቅት እንዳሳለፉት እራሳቸውን እንደ ስደተኛ ተመለከቱ።
"ኢግቦዎችን የማንኛውም የጠፋ ጎሳ ብሎ መጥራት ስድብ ነው። ያንን የሚደግፍ ታሪካዊም ሆነ የአርኪዮሎጂ ማስረጃ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከብዙ ዓመታት በፊት የጄኔቲክ የዘር ሐረግን ለማረጋገጥ ጥረቶች ተደርገዋል። ነገር ግን በዘረ መል ምርመራ የአይሁድ ግንኙነት አልተገኘም።
የአይሁድ የዘር ሐረግ የይገባኛል ጥያቄን የሚወስነው የእስራኤል ራቢኔት ካውንስል የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሊቀመንበር ረቢ ኤሊኤዘር ሲምቻ ዌይዝም እንዲሁ ጥርጥር የላቸውም።
"ከአባታችን ከያዕቆብ ልጆች አንዱ ከጋድ ዘሮች አንዱ ነን ይላሉ። ነገር ግን አያቶቻቸው አይሁዳዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አይችሉም" ብለዋል።
"እነሱ የሚናገሩትን ልማዶችን በተመለከተ የአይሁድ ልምዶችን የያዙ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ማግኘት ይችላሉ።"
የናይጄሪያ አይሁዶች ወደ ይሁዲነት እስካልተቀየሩ ድረስ (የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚያካትት እና ናይጄሪያ ውስጥ በማይገኝ በአይሁድ ፍርድ ቤት ፊት ሲቀርቡ) ዕውቅና አይሰጣቸውም ብለዋል።
ያኮቭ ደግሞ ይህንን የመቀየር ጉዳይ እንደ ስድብ አድርጎ ይመለከተዋል።
"ከተቀየርን እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንቆጠራለን" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Irums
የመገንጠል ማቆጥቆጥ
በጊዮን የሚገኙ ምዕመናን እምነታቸውን አጥብቀው ይከተላሉ። እነሱ እና የናይጄሪያ 12,000 ገደማ የሚገመቱ የአይሁዶች ማህበረሰብ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሌሎች የኦርቶዶክስ አይሁድ ቡድኖች ይደገፋሉ። ልገሳ፣ ጉብኝት እና ዕውቅና እንዲያገኙ ዘመቻ ያደርጋሉ።
አንዱ ታዋቂ ደጋፊያቸው በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን አይሁዶች በሱዳን በኩል በድብቅ ወደ እስራኤል ለመውሰድ በተደረገ ዘመቻ የተካፈሉት የቀድሞው የሞሳድ አባል ዳኒ ሊሞር ናቸው። ከ1980ዎቹ ጀምሮ በናይጄሪያ ያሉትን የአይሁድ ማህበረሰቦችን ጎብኝተዋል። በምዕራብ አፍሪካ የአይሁድ ልምድ የነበረው ከእርስ በርስ ጦርነቱ በፊት እንደነበረ ይከራከራሉ።
ከ500 ዓመታት በፊት ከሞሮኮ መጡ በሚለው አስተሳሰብ ያምናሉ። ይህም ወደ ደቡብ ከመጓዛቸው በፊት መጀመሪያ በቲምቡክቱ ውስጥ ሰፈሩ ይላል። የሚገባቸውንም ዕውቅና ያገኛሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
"የአይሁድ እምነት ከቆዳ ቀለም አልፎ በልብ ውስጥ ነው የሚገኘው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በናይጄሪያ እጅግ ጥንታዊ ነው የተባለው የግዮን ምኩራብ በ1980ዎቹ በኦቫዳይ አቪቻይ እና በክርስቲያ በነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎች ተመሠረተ።
ጓደኛማቾቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን የአይሁድ ሃይማኖት መሠረት መሆኑን ሲገነዘቡ ወደ ይሁዲነት ለመቀየር ወሰኑ።
እሱ ውስጡ ያለው አይሁዳዊ እንደገና እንደታደሰ ተናግሯል። በአይሁድ ልማዶች እና በኢግቦ ወጎች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ሲመለከት የአይሁድ እምነት እውነተኛ መንገድ መሆኑን እርግጠኛ ነበር።
በአቡጃው ጊዮን ምኩራብ አሁን ከሚገኙት ከ 40 በላይ ቤተሰቦች መካከል የተለያዩ ጎሳዎች ድብልቅ ይዟል።

የፎቶው ባለመብት, Irums
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡባዊ ናይጄሪያ ውስጥ እንደ አይሁድ የሚያመልኩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲል አካባቢውን ጠንቅቆ የሚያውቀው የቢቢሲው ቺያጎዚ ንዎንው ተናግሯል።
ለዚህም አብዛኛው ምስጋና እአአ በ2014 የኢግቦን የመገንጠል ዘመቻን እንደገና ለጀመረው የቢያፍራ ተወላጆች (አይፖብ) ይድረስ።
ይህም ተከታዮቻቸው የአይሁድ ዘር መሆናቸውን አስታውሶ እምነቱን እንዲቀበሉ ባበረታታው በናምዲ ካኑ ይመራል። መሪው በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም በሚገኘው የዌስተርን ዎል ሲጸልይ የሚያሳይ ምስል ይፋ ወጥቷል።
ነገር ግን አንዳንድ የአይሁድ እምነት እና የክርስትናን ይዘቶችን በአምልኳቸው ውስጥ በማዋሃድ ከሜሳይኒክ አይሁድ እምነት ጋር በመዛመዱ የእሱ ተከታዮች እንደ ናይጄሪያ ይበልጥ በተቋቋሙ ማህበረሰቦች ውስጥ እንደ እውነተኛ አይሁዶች አይቆጠሩም።
ካኑ አሁን በእስር ላይ ሲሆን በሃገር ክህደት ፍርድ ቤት ቀርቧል። በቅርቡ ነፍጥ ያነሳው ኢፖብ ደግሞ አሸባሪ ቡድን ተብሎ ታግዷል።
"አይፖብ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ሲል በምኩራቡ አለቀስኩ። እንዲህ አልኩኝ 'ይህ ወጣት ልጅ የማንወጣው ችግር ሊያመጣብን ነው። ምክንያቱም አላስፈላጊ ነገር ስለሚያደርግ ነው'አልኩ" ብለዋል የቢያፍራ የቀድሞ ታጋይ አቪቻይ።
የኢፖብ እንቅስቃሴ የ70 ወይም ከዚያ በላይ የአይሁድ ማህበረሰቦች ሠላማዊ አምልኮን አደጋ ላይ ይጥላል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ በደቡብ ምዕራብ አንድ የአይሁድ ማህበረሰብ መሪ ጉባኤዋ ከእስራኤል የመጡ ሦስት ጎብኚዎችን ተቀበላ ለአንድ ወር ስትታሰር ይህ ነገር ተከሰተ።
ጎብኚዎቹ የተለገሱ የቶራ ስጦታዎች (ቶራዎቹ ብዙውን ጊዜ ለአካባቢያዊ ሃይማኖተኞች ለመግዛት በጣም ውድ ናቸው) ርክክብን ለመቅረጽ ነበር የመጡት። ከአይፖብ ጋር ግንኙነት ነበራቸው በሚል ተጠርጥረው ከሃገር ተባርረዋል።
ጊዮን የሚሄዱ አንድ እምነቱ ተከታይ ካኑ ምኩራቡን ለመቀላቀል ባደረገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይነጋራሉ። የኢፖብ ዘመቻ በቅርቡ ወደ ትጥቅ ትግል መዞሩ የአይሁድ እምነት ጽንሰ-ሐሳቦችን የተቃወመ ነው።
ያኮቭ በአይሁድነት ዙሪያ ስላለው ፖለቲካ ፍላጎት የለውም። ለእሱ አስፈላጊው ነገር መንፈሳዊው ገጽታው ነው።
እንደ እሱ ያሉ ኢግቦዎች በእስራኤል በይፋ ዕውቅና ቢሰጣቸው የሃይማኖቱ ማህበረሰብ በናይጄሪያ ውስጥ የበለጠ እንዲደራጅ ይረዳል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ዋና ራባይ የሌለ ሲሆን የኮሸር ምርቶችን (በአይሁድ እምነት የሚፈቀዱ የምግብ ዓይነቶች ናቸው) ማግኘትም ፈታኝ ሊሆን ይችላል።
ብዙውን ጊዜ የሚሸጡትም በአይሁድ ስደተኞች በተያዙ ጥቂት ሱቆች ውስጥ ብቻ ነው። ስለዚህ ማህበረሰቡ የኮሸርን ህጎች ለመከተል እንዲችሉ በአካባቢው የሚመረተውን ይበላል።
ያኮቭ በራቢያዊ ትምህርት ቤት ወይም ልምድ ባለው ራባይ ስር በማጥናት ብቻ ሊከናወን የሚቻለውን ትምህርት ወስዶ የመጀመሪያው ናይጄሪያዊ ራባይ ቢሆን ይወዳል።
"መነሻችንን ለምናውቅ ለእኛ በማንነታችን ጉዳይ እርግጠኞች ነን" ይላል።
"ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች የራሳቸውን ተቀብለው መደገፍ ከቻሉ አይሁዶችም አንዳንድ ማበረታቻዎችን ማሳየት አለባቸው ብዬ አስባለሁ" ሲል ያጠቃልላል።














