የፊሊፒንስ እና የሩሲያ ጋዜጠኞች የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters/Getty
ፊሊፒን-አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳ እና ሩሲያዊው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ሙራቶቭ የ2021 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።
የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሁለቱ ጋዜጠኛች ሽልማቱን ያገኙት ሃሳብን የመግለጽ መብት ለመጠበቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ ነው ብሏል።
ሁለቱ ጋዜጠኞች የተመረጡት ከ329 ዕጩዎች መካከል መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል።
ይህን ከፍተኛ እውቅና ያለውን ሽልማት ያሸነፉት ጋዜጠኞች ኦስሎ በሚገኘው ኖርጄዊያን ኖብል ኢንስቲትዩት ተገኝተው የ1.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይቀበላሉ።
የዘንድሮውን የሰላም ኖቤል ሽልማት ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብለው ተጠብቀው ከነበሩት መካከል የአከባቢ ጥበቃ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ፣ የመገናኛ ብዙሃን መብት ተከራካሪ ድርጅት የሆነው ሪፖርተርስ ዊዛአውት ቦርደርስ እና የዓለም ጤና ድርጅት ይገኙበታል።
የፊሊፒን እና የአሜሪካ ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ማሪያ ሬሳ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን ማርማሪ ዘጋቢ ሆና ሰርታለች።
እአአ 2020 ላይ ማሪያ የፊሊፒንስ የሳይበር ሕግ ተላልፋለች በሚል በፊሊፒንስ መንግሥት ክስ ተመስርቶባት ነበር።
ተቺዎች ግን የፊሊፒንስ መንግሥት ክስ የመሰረተባት የጋዜጠኝነት ሥራዋን ለማስቆም እንጂ የተላለፈችው ሕግ ኖሮ አይደለም ይላሉ።
ሩሲያዊው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ሙራቶቭ ከሌሎች ጋር በመሆን የመሰረተው 'ኖቫጃ' ጋዜጣ በሩሲያ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን አስጠብቆ ቆይቷል ብሏል የኖቤል የሰላም ሽልማት ድርጅት።












