ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በትግራይ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ በእጅጉ ንሯል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, UNFPA/Sufian Abdul-Mouty
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባባሪ ጽ/ቤት (ኦቻ) ከሰኔ አጋማሽ አንስቶ በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መናሩን ገለጸ።
እንደ ጽህፈት ቤቱ መግለጫ ከሆነ በክልሉ "የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እጥረት ፈታኝ ሆኗል።"
በተጨማሪም በአይደር ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሕጻንን ጨምሮ 18 ሰዎች ሄሞዲያሊሲስ ካቲተር በማጣታቸው መሞታቸውን የኦቻ ሪፖርት ያሳያል።
ኦቻ በሪፖርቱ በሽረ የነዳጅ ዋጋ 2,300 ፐርሰንት የጨመረ ሲሆን፤ በመቀለ እና በሌሎች ከተሞችም ገበያ ላይ የአስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት ተከስቷል ብሏል።
"መሠረታዊ የምግብ እና ሌሎችም አስፈላጊ ቁሳቁሶች ዋጋ መናር ነዋሪዎችን እየፈተነ ነው። ሥራቸውን ያጡ አቅመ ደካማ ሰዎች የመግዛት አቅማቸው ቀንሷል" ብሏል ድርጅቱ።
በተለይም ከሰኔ ወዲህ ሲቪል ሠራተኞች እና ሌሎችም ተቀጣሪዎች ደሞዛቸው ስለተቋረጠ መሠረታዊ አቅርቦት ለማሟላት ተቸግረዋል።
በባንኮች በቂ ገንዘብ ባለመኖሩ፤ ከነዋሪዎች በተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችም ለወራት ደመወዝ እንዳልወሰዱ ኦቻ አስታውቋል።
"ታማኝ ሪፖርቶች እንደጠቆሙን ከሆነ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ምግብ ነክ ያልሆኑ እና በእርዳታ የተሰጧቸው ቁሳቁሶችን እየሸጡ ምግብ እየገዙ ነው" ብሏል።
በሌላ በኩል በአጎራባቾቹ የአማራ እና አፋር ክልሎችም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የኦቻ ሪፖርት ያሳያል።
በአማራ ክልል ከሰሜን ጎንደር፣ ከማዕከላዊ ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከደቡብ ወሎ እና ከአዊ ዞኖች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አፋጣኝ እርዳታ ያሻቸዋል።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን የፈተነው የነዳጅ እጥረት
ኦቻ ኢትዮጵያ ባወጣው ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁሟል።
እአአ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ የሰበሰበውን መረጃ ትናንት መስከረም 27፣ 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ሪፖርት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከሰተውን አስቀድሞ ለመገመት አዳጋች እየሆነ እንደመጣም አክሏል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት እንደጨመረ እና ጦርነቱ ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከተስፋፋ ወዲህ ድጋፍ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር እንደናረ ገልጿል።
ከትግራይ ክልል 75 በመቶ ያህል አካባቢ ለእርዳታ ተደራሽ ቢሆንም፤ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነው ሰሜናዊ ክፍል፣ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ በኩል የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ስላልሆነ እስካሁን እርዳታ ለመስጠት አለመቻሉን ኦቻ ጠቁሟል። በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ያለው የነዳጅ እና የገንዘብ እጥረት የእርዳታ አቅርቦትን እንዳስተጓጎለ በሪፖተርቱ ተጠቅሷል።
በአፋር ክልል በኩል ከሰመራ ወደ አቤላ ከዚያም ወደ መቀለ የሚወስደው መንገድ ብቻ ለእርዳታ ክፍት መደረጉ ሂደቱን እንዳስተጓጎለ ኦቻ አክሏል።
በአማራ እና በአፋር ክልሎች አሁንም ድረስ ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ስላሉ እርዳታ ለማቅረብ ፈተና እንደገጠመው ድርጅቱ አስታውቋል።
እአአ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በአፋር በኩል 80 የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ገብተዋል።
ከሐምሌ ወዲህ ወደ ክልሉ የተላኩ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአጠቃላይ 686 ናቸው። ይህም አጠቃላይ ከሚፈለገው 12 በመቶ ብቻ ነው።
ኦቻ በላካቸው 80 ተሽከርካሪዎች ማድረስ የቻለው ምግብ፣ ውሃ፣ አልሚ ምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ነው።
"ሆኖም ግን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች እና ነዳጅ ለመውሰድ አልተፈቀደልንም" ሲል በሪፖርቱ አስፍሯል።
ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ትግራይ ነዳጅ የተላከው ከዘጠኝ ሳምንታት በፊት እንደነበረና አሁን ላይ ስምንት ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ሰመራ ላይ ከመንግሥት ፍቃድ እስኪሰጣቸው እየተጠባበቁ መሆኑን ድርጅቱ አክሏል።
የተከሰተው የነዳጅ እጥረት የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎችን ሥራ እንዳደናቀፈ ኦቻ ሳይጠቅስ አላለፈም።
የረድዔት ድርጅቶች እንደሚሉት በክልሉ ያለውን የእርዳታ ፍላጎት ለማሟላት በየቀኑ 100 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች መድረስ አለባቸው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ሕብረት ለሁለተኛ ጊዜ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖችን ወደ ትግራይ መላኩን አስታውቋል።
ከሁለት ቀናት በፊት መቀለ የደረሰው አውሮፕላን 10.6 ቶን ሕይወት አድን የእርዳታ አቅርቦት ነው። ይህም ለሕጻናት የሚውል 4.4 ቶን አልሚ ምግብን ይጨምራል።
እርዳታው ዩኒሴፍ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለገጠማቸው ሕጻናት ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንታት የሚውል ምግብ እንዲያቀርብ ያስችላል።
ለሦስት ወራት ያህል ለ280 ሺህ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ማቅረብ የሚያስችል እርዳታም በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ ውስጥ ተካቷል።
"ቤት ውስጥ የወለዱ እናቶች ሞተዋል"
"የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እጥረት ፈታኝ ሆኗል። አይደር ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሕጻንን ጨምሮ 18 ሰዎች ሄሞዲያሊሲስ ካቲተር በማጣታቸው ሞተዋል" ይላል የኦቻ ሪፖርት።
የሕክምና መሣሪያው በአፋጣኝ ካልደረሰ ተጨማሪ 34 ሰዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉም ብሏል።
በአይደር ሆስፒታል የኦክስጅን ማሽን እንደተሰበረና ማሽኑን ለመጠገን የሚሆን መለዋወጫ በክልሉ እንደሌለ ተገልጿል።
በሪፖርቱ መሠረት፤ ሰልዋ በተባለ ወረዳ አምስት እናቶች ቤት ውስጥ ሲወልዱ ሕይወታቸው አልፏል።
በሀውዜን፣ በአክሱም፣ በአዲግራት እና በሌሎችም ከተሞች የሚገኙ ሆስፒታሎች የተመጣጣኝ ምግብ እጥረትን ለማከም አልቻሉም ተብሏል።
"የነዳጅ፣ የገንዘብ እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት በመኖሩ በ10 ወረዳዎች አሁን ላይ አገልግሎት ማግኘት የተቻለው በ13 የጤና ተቋማት እና 39 የስደተኛ ጣቢያዎችን ነው" ይላል የኦቻ ሪፖርት።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለመቀጠል በየሳምንቱ 6.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
ይህም ሊሳካ የሚችለው ባንክ በአግባቡ አገልግሎት ሲሰጥ ወይም መንግሥት በቂ ገንዘብ እንዲዘዋወር ሲፈቅድ ነው።
ከሐምሌ 12 ወዲህ 4 ሚሊዮን ዶላር (ወደ 189 ሚሊዮን ብር ገደማ) ወደ ትግራይ እንዲገባ ተፈቅዷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መርሕ መሠረት፤ የረድዔት ድርጅቶች በሰብአዊ በረራ ወቅት ወደ ትግራይ መውሰድ የሚችሉት 432,000 ሚሊዮን ዶላር (2 ሚሊዮን ብር ገደማ) ነው።
ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ በሳምንት ሁለት የሰብአዊ እርዳታ አውሮፕላኖች የሚበሩ ሲሆን፤ ከሐምሌ ወዲህ 19 በረራዎች ተካሂደዋል።












