የሳዑዲው ኩባንያ የእንግሊዙ ኒውካስትል እግር ኳስ ክለብን ገዛ

የኒውካስትል ዩናይትድ ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳዑዲ አራቢያ የኩባንያዎች ጥምረት የእንግሊዙን ኒውካስትል ዩናይትድ በ305 ሚሊዮን ፓውንድ መግዛቱ ተገለጸ።

ፕሪሚዬር ሊጉ ኒውካስትል ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብ ተላለፎ እንዲሰጥ የወሰነው የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ እንደማይገባ ከስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ነው።

ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ የተሰኘው ጥምረት 80 በመቶ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ከመንግሥት ጋር ሳይነካካ በራሱ ነው የሚንቀሳቀሰው ተብሏል።

ነገር ግን የሳዑዲ አራቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ አለቃ ናቸው።

ኒውካስትል የዚህ ጥምረት ንብረት የሆነው የግዢው ስምምነት በፕሪሚዬር ሊጉ ባለንብረቶችና ዳይሬክተሮች ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው።

ላለፉት 14 ዓመታት ኒውካስትል ዩናይትድን የግል ንብረታቸው አድርገው ሲቆጣጠሩ የነበሩት ማይክ አሽሊ ከቡድኑ ጋር ተለያይተዋል።

ከዜናው በኋላ የቡድኑ ደጋፊዎች በሴይንት ጄምስ ፓርክ ስታድዬም ዙሪያ ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።

ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ 250 ቢሊዮን ፓውንድ የሚገመት ሃብት ያለው ሲሆን ኒውካስትልም ከዓለማችን ውድ ክለቦች አንዱ መሆን ችሏል።

ጥምረቱን አናግረው ግዢውን እውን ያደረጉት የፋይናንስ ባለሙያው አማንዳ ስታቭሊ አዲሶቹ የክለቡ ባለቤቶች የረዥም ጊዜ ዕቅድ ያላቸው ሲሆን ኒውካስትልን የዋንጫ ባለቤት ለማድረግ አልመዋል ይላሉ።

ኒውካስትል ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳው በፈረንጆቹ 1995 በተካሄደው የኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ላይ ነበር።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ባወጣው መግለጫ ፈንዱ ኒውካስትልን ለመግዛት አጋጥሞት የነበረውን አነጋጋሪ ጉዳይ ፈቷል ብሏል።

አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ ክለቡ ከተሸጠ በኋላ ባለቤትነቱ የማን ይሆናል የሚለው ሲሆን አሁን በተደረሰው ስምምነት መሠረት ፈንዱ ኒውካስትልን በተመለከተ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አይኖረውም ይላል የፕሪሚዬር ሊጉ መግለጫ።

የኒውካስትል ደጋፊዎች "እኛ የምንሻው ክለባችን እንዲያሸንፍ ሳይሆን ቢያንስ እንዲሞክር ነው" የሚል መፈክር አንግበው ስታድየማቸው አካባቢ ታይተዋል።

ኒውካስትል በማይክ አሽሊ ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ለአህጉር አቀፍ ውድድር ማለፍ የቻለው።

የኒናስትል ዩናይትድ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኒናስትል ዩናይትድ ደጋፊዎች

ክለቡና ፈንዱ ባለፈው ዓመት ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ፕሪሚዬር ሊጉ ክለቡን ማን ነው የሚገዛው በሚል ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል በማለቱ ምክንያት ተቋርጦ ነበር።

የቢቢሲ ስፖርት ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳዳሪዎችና ጥምረቱ ዜናው ይፋ ከሆነበር ዕለተ ረቡዕ አስቀድመው ከስምምነት ደርሰው ነበር።

የሳዑዲ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደርሳል የሚሉ ወቀሳዎች በተደጋጋሚ ስለሚበሱበት ነው ፕሪሚዬር ሊጉ መንግሥት በስምምነቱ ጣልቃ እንዲገባ ያልፈለገው።

ምዕራባዊያን የስለላ ድርጅቶች የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋዜጠኛ ጃምል ኻሾግጂ እንዲገደል አዘዋል ሲሉ ይወቅሳሉ። ልዑሉ ደግሞ እጄ የለበትም ይላሉ።

አንዳንድ ለሰብዓዊ መብት ክብር ቆመናል የሚሉ ድርጅቶች ኒውካስትል የሳዑዲ አራቢያ ኩባንያዎች ጥምረት ንብረት መሆኑን ተቃውመውታል። ከእነዚህ መካከል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የዩናይት ኪንግደም ቅርንጫፍ አንዱ ነው።

ኒውካስትል በያዝነው የውድድር ዘመን ሰባት ጨዋታዎችን አድርጎ አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ በሰንጠረዡ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አሠልጣኝ ስቲቭ ብሩስ ሊባረሩ ይችላሉ የሚሉ ዜናዎች በስፋት እየተሰራጩ ነው።