የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያ አላጓጓዝኩም ሲል የቀረበበትን ከስ አጣጣለ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጦር መሣሪያዎችን አጓጉዛል ሲል ሲኤንኤን ያወጣውን ዘገባ አየር መንገዱ አስተባበለ።
የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትግራዩ ጦርነት በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ አጓጉዟል ሲል የሰው እና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ ዘገባ ስርቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የጦር መሳሪያዎችን አላጓጓዝኩም ሲል የሲኤንኤን ዘገባን አጥብቆ የተቃወመ ሲሆን የሲኤንኤን ዘገባ ማስተካከያ እንዲደረግበትም ጠይቋል።
". . . አየር መንገዱ በየትኛውም አውሮፕላኑ ወደየትኛወም መዳረሻው የትኛወንም የጦር መሳሪያ አላጓጓዘም" ብሏል አየር መንደጉ ባወጣው መግለጫ።
በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማሸነፉን ያስታወሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርን (አይኤቲኤ) ሕጎችን ጨምሮ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ደንቦችን በጥብቅ እንደሚከተል አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ በማንነታቸው ብቻ ከሥራ ገበታቸው የታገዱ ወይም የተባረሩ ሠራተኞች የሉም ብሏል።
ይህንም ከአየር መንገዱ የሰው ሃብት ማረጋገጥ ይችላል በማለት አየር መንገዱ የሲኤንኤን ዘገባን ተከትሎ ባወጣው መግለጫው ላይ ተቅሷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በተያያዘ ዜና አየር መንገዱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ እንደነበረ እና በገጹ የተላለፈው መረጃ ከድርጅቱ እውቅና ውጪ እንደሆነ አስታውቋል።
አየር መንገዱ በፌስቡክ ገጹ ላይ ከድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተላለፈ ነው ተብሎ የተጋራው መረጃ ሐሰተኛ ነው ያለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የፌስቡክ ገጹ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እንደሚገኝ ገልጿል።
የሲኤንሴን ዘገባ ምን ይላል?
ከትናንት በስቲያ ሲኤንኤን ባወጣው ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲቪል አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ከተሞች መካከል ጦር መሳሪያዎችን ማጓጓዙን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ሲኤንኤን በዘገባው ያጋራው ሰዎች ጦር መሳሪያዎችን ሲጭኑ ያሚያሳይ ምስል የተነሳው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ስለመሆኑ አረጋግጫለሁም ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ሲኤንኤን በዘገባው፤ አየር መንገዱ የጦር መሳሪያዎቹን ላጓጓዘበት ከመከላከያ ሚኒስቴር ክፍያ የጠየቀበትን ስነድ፣ የጭነት አይነት እና መዳረሻ የሚያሳዩ የአየር ጉዞ ሰነዶችን (ኤር ዌይቢልስ) አቅርቧል።
በሲኤንኤን ዘገባ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የዘረፉ ባለሙያዎች አየር መንገዱ የጦር መሳሪያዎችን ማጓጓዙ የአቪዬሽን ሕግጋትን ይተላለፋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ስሙ ሲነሳ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያዎችን እና ወታደሮችን ወደ ትግራይ ክልል በማጓጓዝ ላይ ይገኛል በሚል በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ መረጃዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ አየር መንገዱ ክሶቹን "መሠረተ ቢስ" ናቸው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።
አየር መንገዱ በወቅቱ ባወጣው መግለጫው የትግራይ የአየር ክልል ዝግ ሆነው በቆየበት ወቅት ወደ ክልሉ በረራ አለማድረጉንም ግልጾ ነበር።
ባለው የደኅንነት ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቅ የገለጸው አየር መንገዱ፤ "መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች የአየር መንገዱን ከፍተኛ ዝና ለማጠልሸት እየሠሩ ነው" ሲል ወቅሷል።
"የእኛን ስም ለማጠልሸት የተለያዩ የፎቶ ቅንብሮችን፣ የድሮ እና የማይዛመዱ ሥዕሎችን ተጠቅመዋል" ብሏል።












