በሚኒስትርነት ስለተሾሙት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምን እናውቃለን?

ፎቶዎች

አዲስ በተመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃዋሚ አመራሮች በሚኒስትርነት ተሹመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው እንዲሾሙ ካደረጓቸው 22 ሚኒስትሮች መካከል ሦስቱ ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመጡ ናቸው።

ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ አቶ በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና አቶ ቀጀላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር፣ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ናቸው።

እነዚህ ሦስት ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወጣትተው በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ስለተካተቱት ግለሰቦች ምን እናውቃለን?

መስመር

አቶ በለጠ ሞላ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር [የአብን ሊቀመንበር]

በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ካቢኔ ውስጥ ቦታን ካገኙት ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ፣ በአማራ ክልል ሠሜን ወሎ ቆቦ ከተማ ውስጥ ነው ተወለዱ።

አቶ በለጠ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የተመረቁ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፍልስፍና እንዲሁም በአፕላይድ ኤቲክስ አግኝተዋል።

አቶ በለጠ ሞላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ትምርት ክፍል መምህር የነበሩ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መስራችም ናቸው።

በለጠ ሞላ በ2009 ዓ.ም በጀርመን አገር በሚገኘው ቱቢንጉን ዩኒቨርስቲ ተጋባዥ ተመራማሪ በመሆንም አገልገለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን አባል በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

አብን ከተመሰረተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የመጀመሪያው ምርጫ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አምስት መቀመጫዎችን ለማግኘት ችሏል።

ፓርቲው በአማራ ክልል ምክር ቤት ውስጥም ከአስር በላይ መቀመጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በተመሰረተው በአማራ ክልል መስተዳደር ውስጥም አንድ አመራሩ በቢሮ ኃላፊነት ተሹመዋል።

መስመር

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ፣ የትምህርት ሚኒስትር [የኢዜማ መሪ]

በቢሸፍቱ ከተማ የተወለዱት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የፖለቲካ ተሳፏቸው የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ኢሕአፓን ውስጥ ሲሆን፤ ቀይ ሽብር ከመጀመሩ በፊት ወደ በረሃ ወጥተው ሁለት ዓመት በትግል ቆይተዋል።

ከዚያም ወደ ሱዳንና አሜሪካ ተሰደው በአሜሪካም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒው ዮርክ በኢኮኖሚክስ፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከኒው ስኩል ፎር ሶሻል ሪሰርች አግኝተዋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የማኅበሩ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር በመሆን አገለግለዋል።

ብርሃኑ (ፕ/ር) በ1994 (እአአ) ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በማስተማርና ሌሎች ሥራዎች ቆይተው ከሌሎች ጋር በመሆን ቀስተ ደመና የተባለውን ፓርቲ መስርተው ብዙም ሳይቆዩ ተቃዋሚዎች ጥምረት የሆነው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲመሰረት ጉልህ ሚና ነበራቸው።

በ97ቱ ምርጫም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልነት ተመርጠው የከተማዋ ከንቲባ እንዲሆኑ ታጭተውም ነበር። በምርጫው ሰበብ የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ የቅንጅት አመራሮች ሲታሰሩ ብርሃኑ ነጋም ለእስር ተዳገው ነበር።

ከእስር ሲፈቱ ወደ አሜሪካ ተመልሰው በወቅቱ የነበረውን መንግሥት በሁሉም የትግል አማራጮች የመታገል አላማው ያደረገውን የግንቦት 7 ንቅናቄን ከመሰረቱት አንዱ ሲሆኑ ሊቀመንበር በመሆንም በትጥቅ ትግል ላይ የነበረውን ቡድን መርተዋል።

ብርሃኑ ነጋ በፖለቲካና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጽሁፎችን ያበረከቱ ሲሆን፤ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ሳሉ "የነፃነት ጎሕ ሲቀድ" እና በስደት ላይ ሳሉ ደግሞ "ዴሞክራሲ እና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ" የሚሉ ሁለት መጽሐፎች አሳትመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ወደ አገር ቤት ተመለሰ። ከዚያም የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተዋሃዱበት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እንዲመሰረት ጉልህ ሚና ተጫውተው የፓርቲው መሪ ለመሆን ችለዋል።

መስመር

አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር [የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር]

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ቂልጡ ካራ ነው።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ትምህርት ያገኙት አቶ ቀጀላ፣ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ በተያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ቢቂላ አራርሳ በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የቢሮ ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ምክትል የሆኑት አቶ ቀጀላ በሚኒስትርነት መሾማቸው በወቅቱ ተገልጿል።

አቶ ቀጀላ መርዳሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በካቢኔያቸው ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ማካተታቸው በጋራ አገሪቷን ወደፊት ለማራመድ የተወሰደ እርምጃ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ መደሰታቸውን የገለፁት አቶ ቀጀላ፣ ፓርቲያቸው በምርጫ ለመሳተፍ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አቶ ቀጀላ በኦነግ ውስጥ በነበረው ችግር እና በምርጫ ቦርድ በኩል በተፈጠረው መጓተት በምርጫው ሳይወዳደሩ መቅረታቸውን ይናገራሉ።

ኦነግ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተሳትፎ ቢሆን ኖሮ በኦሮሚያ ድምጽ አግኝቶ በርካታ የፓርላማ ወንበሮችን ያገኝ ነበር ያሉት አቶ ቀጀላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን በመረዳት ይመስላል ለማሳተፍ የወሰኑት ብለዋል።

አቶ ቀጀላ ለአገር ይጠቅማል፣ ወደፊት ያራምደናል ብዬ የማምናቸውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆኔን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ ብለዋል።

ሕዝቡን ማገልገል እፈልጋለሁ ያሉት አቶ ቀጀላ፣ ያሉትን ፖሊሲዎች ለማስፈፀም፣ አስፈላጊ የሆኑ ሪፎርሞችን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመስራት ስላላቸው ዝግጁነት ሲናገሩ፣ በተመደብኩበት ዘርፍ ላይ ክፍተቶች ካሉ እነዚያ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ የማቀርበው ሃሳብ ይስተናገዳል ብዬ አምናለሁ ሲሉ አክለዋል።