ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሦስት የተቃዋሚ አባላትን በካቢኔያቸው ውስጥ አካተቱ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲሱ ካቢኔያቸው ውስጥ ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በሚኒስተርነት እንዲያገለግሉ ለሕዝብ ተወካዮች አቅርበው አስሹመዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በሚኒስትር ተሹመዋል።
ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፣ አቶ በለጠ ሞላ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ እንዲሁም አቶ ቀጀላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ተካተዋል።
ኢዜማ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን የአብረን እንሥራ ጥያቄ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ጥያቄውን ተቀብሎ አብሮ ለመሥራት በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ባሳለፍነው እሁድ አስታውቋል።
ኢዜማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አራት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን አብን ደግሞ አምስት መቀመጫዎችን ለማሸነፍ ችሏል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ከግንባሩ ተለይቶ በመውጣት በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመራው ግንባር በምርጫው ባይሳተፍም ምክትሩ በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ተካተዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ባለፈው ሳምንት ሥራውን በጀመር ወቅት በከንቲባነት የተሾሙት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ 26 የካቢኔ አባሎቻቸውን አቅርበው ሲያስሾሙ ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮችን አካተው ነበር።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅብራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር የሱፍ ኢብራሂም ደግሞ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ሆነው ተሹመዋል።
የኦሮሚያ ክልልም ከሳምንት በፊት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ አራርሳ ቢቂላን የቢሮ ኃላፊ አድርጎ የሾመ ሲሆን የአማር ክልልም ከተቃዋሚዎቹ አብንና ከአዴኃን ሁለት ሰዎችን በቢሮ ኃላፊነት ሹመት ሰጥተዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ እጩ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሾሙ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ አባላት እና ኃላፊነቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው።
- ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር
- አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር
- አሕመድ ሽዴ የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር
- ሙፈሪያት ካሚል የስራ እና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር
- ኡመር ሁሴን ኦባ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር
- አይሻ ሞሐመድ (ኢንጂነር) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር
- ሀብታሙ ኢተፋ ገለታ (ኢንጂነር) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር
- ዳግማዊት ሞገስ በቀለ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር
- ገ/መስቀል ጫላ ሞጣሎ የንግድ እና ቀጣና ትስስር ሚኒስቴር ሚንስትር
- መላኩ አለበል አዲስ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር
- ብናልፍ አንዱዓለም የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር
- ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር
- ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገ/መድህን የጤና ሚንስትር
- አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር
- ላዕቀ አያሌው አንተነህ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር
- ጫልቱ ሳኒ ኢብራሂም የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር
- ታከለ ኡማ በንቲ የማዕድን ሚኒስቴር ሚንስትር
- ፍጹም አሰፋ አዴላ (ዶ/ር) የፕላን ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር
- ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
















