ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የካቢኔ አባላቶቻቸውን አስሾሙ

ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ እጩ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሾሙ።
የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካላት ያደራጃል፤ ይመራል በማለት የፖለቲካ ስልጣን ይሰጣል።
በዚህ መሠረት በፓርቲያቸው ለጠቅላይ ሚንስትርነት ታጭተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የካቢኔዎቻቸውን አባላት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው በጠቅላይ ሚንስትሩ የቀረቡትን ሹመቶች በ2 ተቃውሞ እና 12 ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በጠቅላይ ሚንስትሩ የቀረቡ የካቢኔ አባላት እና ኃላፊነቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው።
1.ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር
2.አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር
3.አሕመድ ሽዴ የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር
4.ሙፈሪያት ካሚል የስራ እና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር
5.ኡመር ሁሴን ኦባ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር
6.አይሻ ሞሐመድ (ኢንጂነር) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር
7.ሀብታሙ ኢተፋ ገለታ (ኢንጂነር) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር
8.ብርሃኑ ነጋ ቦንገር የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር
9.ዳግማዊት ሞገስ በቀለ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር
10.ገ/መስቀል ጫላ ሞጣሎ የንግድ እና ቀጣና ትስስር ሚኒስቴር ሚንስትር
11.መላኩ አለበል አዲስ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር
12.ብናልፍ አንዱዓለም የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር
13.ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር
14.ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገ/መድህን የጤና ሚንስትር
15.በለጠ ሞላ ጌታሁን የኢኖቬሸን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር
16.አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር
17.ላዕቀ አያሌው አንተነህ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር
18.ጫልቱ ሳኒ ኢብራሂም የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር
19.ታከለ ኡማ በንቲ የማዕድን ሚኒስቴር ሚንስትር
20.ፍጹም አሰፋ አዴላ (ዶ/ር) የፕላን ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር
21.ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
22.መርዳሳ ቱሉ የባህል እና ስፖርት ሚንስቴር ሚንስትር
መስፈርቶች
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ የካቢኔ አባላት እጩዎቻቸውን ባቀረቡበት ምክንያት መመዘኛዎች ተናግረዋል።
ከመመዘኛዎች ውስጥ የፖለቲካ ልዩነት ችግር አለመሆኑን ጠቅላይ ሚንሰትሩ ተናግረዋል። "ለአገር ልማት አብረን መስራት እንችላለን" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
የትውልድ ቦታ እና ኃይማኖት ታሳቢ በካቢኔ ሹመት ውስጥ ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል። ልምድ፣ ብቃት እና የመፈጸም አቅም እንዲሁም የጾታ ተዋጽኦ ስብጥር ታሳቢ ለማድረግ መሞከሩንም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የአዲሶቹ የካቢኔ አባላት ዋና ተልዕኮ "ሌብነት እና ልመናን ማጥፋት ነው" ብለዋል።
የካቢኔ አባላት የኢትዮጵያ ተወካይ እንጂ የብሄር ተወካይ አይደላችሁም ብለዋል። "አንድ ሰው የግብርና ሚንስትር ከሆነ ለአንድ አካባቢ ተወክሎ የሚሰራ ከሆነ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመፍጥር ችግር ይሆናል" ብለዋል።
"የብሔር ተወካይ መሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ልክ ነው በሚኒስትሮች ካቢኔ ግን አይሰራም" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።












