ታይዋን 38 የቻይና ተዋጊ ጀቶች የአየር ክልሏን አልፈው መግባታቸውን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታይዋን 38 ንብረትነታቸው የቻይና የሆኑ ተዋጊ ጀቶች የአየር ክልሏን አቋርጠው መግባታቸውን እና ይህም በቤይጂንግ የተፈፀመባት ትልቁ ወረራ መሆኑን አስታወቀች።
የታይዋን የመከላከያ ሚኒስትር እንዳሉት በሁለት ዙር ወደ አየር ክልሏ ከገቡት አውሮፕላኖች ውስጥ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ መተኮስ የሚችሉም ይገኙበታል።
ታይዋን በበኩሏ የሚሳኤል ሥርዓቷን በማሰማራት ብሎም ጀቶቿን በማሰባሰብ ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነች።
ቻይና የዴሞክራሲ ሥርዓት የምትከተለውን ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ ብትቆጥርም ታይዋን ግን ራሷን እንደ ሉአላዊ አገር ትቆጥራለች።
ታይዋን ከአንድ ዓመት በላይ የቻይና አየር ኃይል በግዛቷ አካባቢ የተለያዩ ግዳጆችን ሲያከናውን እንደነበረ አቤቱታዋን ስታሰማ ቆይታለች።
የታይዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ቼንግ ቻንግ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ቻይና የአካባቢያዊ ሰላምን በመረበሽ በወታደራዊ ጥቃት ተሳትፋለች" ብለዋል።
የቻይና ሕዝቦች ሪፐብሊክ ከተመሰረተ 72 ዓመቱን የሚያከብረው የቻይና መንግሥት እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ባጋጠሙ ተመሳሳይ ክስተቶች ወቅት እንዲህ ያሉ በረራዎች ሉአላዊነቷን ለመጠበቅ እና አሜሪካ እና ታይዋን የፈጠሩት ጥምረት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ቤይጂንግ ስትገልጽ ቆይታለች።
የታይዋን የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ 25 ንብረትነታቸው የቻይና ሕዝቦች ነጻነት ሠራዊት የሆኑ አውሮፕላኖች በጠራራ ጸሐይ በደቡብ ምዕራብ የሚገኘውን የግዛቲቱን የአየር መከላከያ ዞን ጥሰው መግባታቸውን አስታውቋል።
ይህ ዞን ከታይዋን ድንበር ውጪ የሚገኝ ሲሆን አካባቢው የውጪ አውሮፕላኖችን ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል የመለየት እና የመቆጣጠር ሥራ የሚሰራበት ዞን ነው። አካባቢው የዓለም አቀፍ የአየር ክልል አካልም ነው።
ይህንን ተከትሎም 13 የቻይና አውሮፕላኖች አርብ አመሻሽ ላይ ወደ ታይዋን የበረሩ ሲሆን በታይዋን እና በፊሊፒንስ መካከል ባሉ የውሃ አካላት ላይ ማንዣበባቸው ተነግሯል።












