አፍጋኒስታን፡ ባይደን አሜሪካዊያንን ከካቡል የማስወጣት ተግባር ከስጋት ነጻ አይደለም አሉ

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን መግለጫ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል እየተካሄደ ያለው ሰዎችን ከአገሪቱ የማስወጣት ተግባር "ከአደጋ ሙሉ በሙሉ ነጻ አይደለም" ሲሉ ገለጹ።

ባይደን በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ እስካሁን ድረስ 13,000 ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷን ብሎም ይህ በታሪክ ትልቁ እንዲሁም አስቸጋሪው እንደሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካ እያካሄደችው ያለው ዜጎቿን በአየር የማስወጣት ዘመቻ በታሊባን እንቅፋት እየገጠመው አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል። ይህም ከመከላከያ ኃላፊያቸው ጋር የተቃረነ ንግግር መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል።

ፕሬዝዳንቱ ታሊባን አፍጋኒስታንን በአጭር ጊዜ መቆጣጠሩን ተከትሎ ከመላው ዓለም የተለያየ ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።

የእረፍት ጊዜያቸውን አቋርጠው ወደ ሥራ የተመለሱት ባይደን "ወደ አገራችሁ መመለስ የሚፈልጉ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ቤታችሁ እንመልሳችኋለን" ብለዋል።

ከአሜሪካዊያን በተጨማሪም ከ50 እስከ 65 ሺህ የሚደርሱ ከአሜሪካ ጋር ሲሰሩ የነበሩ አፍጋኒስታናውያንንም ለማስወጣት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዳለ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

"አትሳሳቱ ይህ ሰዎችን የማስወጣት ተልዕኮ አደገኛ ነው። ለጦር ኃይሎቻችን አደጋን የጋረጠ ብሎም እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየተካሄደ ያለ ተግባር ነው" ብለዋል።

"የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ወይም ያለ ምንም አደጋ እንደሚጠናቀቅ አሁን ቃል መግባት አልችልም። ነገር ግን የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆኔ አስፈላጊውን ሁሉ ሀብት እንደማሰባስብ አረጋግጣለሁ" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።

ታሊባን የአሜሪካን ፓስፖርት የያዘ ማንኛውም ሰው ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዲገባ እየፈቀደ መሆኑን በመጥቀስ የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ካቡል መላክ አስፈላጊ አይሆንም ብለዋል።

ነገር ግን ከካቡል እየወጡ ያሉ በርካታ ዘገባዎች የአሜሪካ ዜጎች ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ለመግባት እንቅፋቶች እየገጠማቸው እንደሆነ ያመላክታሉ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን አርብ ዕለት ለሕግ አውጪዎች እንደተናገሩት አሜሪካውያን አፍጋኒስታንን ለመልቀቅ በሚሞክሩበት ወቅት በታሊባን ታጣቂዎች እንደተደበደቡ መግለጻቸውን ፖለቲኮ ዘግቧል።