ዛኪ አንዋር ፡ አውሮፕላን ላይ ተንጠልጥሎ ከአገር ለመውጣት የሞከረው አፍጋኒስታናዊ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, AFGHAN SPORTS SOCIETY
የታሊባንን ካቡል መግባት ተከትሎ በአየር ጣቢያ ከተገኙ አፍጋኒስታዊያን መሀል አንዱ ዛኪ አንዋር ነበር፡፡
ዛኪ ገና የ19 ዓመት ወጣት ሲሆን ለአፍጋኒስታን ወጣት ብሔራዊ ቡድን ኳስ ተጫዋች ሆኖ ለአገሩ ተሰልፎ ያውቃል፡፡
ይህ ወጣት በአውሮፕላን ተንጠላጥሎ ከአገር ለመውጣት ሲሞክር ከአየር ላይ ወድቆ ሕይወቱ ልታልፍ ችላለች፡፡
የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት የዚህን ወጣት ማንነት መለየት ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ሰዓታት የአሟሟቱን ሁኔታም ሆነ እንዴት በአውሮፕላኑ ሊንጠላጠል ቻለ የሚለውን በዝርዝር ማወቅ አልቻሉም፡፡
ታሊባን ካቡል መግባቱን ተከትሎ በሺህ የሚቆጠሩ የአፍጋን ዜጎች በአየር ጣቢያ ተገኝተው አገር ለመልቀቅ ሲተረማመሱ ታይተዋል፡፡
በተለይም የምዕራብ አገራት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት በሚሯሯጡበት በዚያ አስጨናቂ ወቅት ከምዕራባዊያን ዜጎች ጋር አገር ለመልቀቅ አፍጋናዊያን የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
ሰኞ ዕለት የወጡ ምሥሎች እንዳረጋገጡት በአየር ጣቢያ የአውሮፕላን መንደርደሪያ በሺህ የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናዊያን የአሜሪካ ኤር ፎርስ አውሮፕላንን ከበው ሲዋከቡ ታይተዋል፡፡ አንዳንድ ዜጎችም በአውሮፕላኑ ጎን፣ በአውሮፕላኑ ክንፍና ጎማ ለመወጣጣት የተቻላቸውን ሲያደርጉ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የአገሬው ሚዲያ እንደዘገበው ቢያንስ ሁለት ሰዎች ከተነሳው አውሮፕላን ላይ ቁልቁል ተፈጥፍጠዋል፡፡
ከዚህ ሌላ የአሜሪካ ኤር ፎርስ ኳታር ሲያርፍ በአውሮፕላኑ የማረፊያ ክንፍ ውስጥ የሞተ ሰው አስክሬን ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዛኪ አንዋር ከአውሮፕላን ተፈጥፍጦ መሞት ከተሰማ በኋላ በፌስቡክ ሐዘናቸውን ከገለጹት ተቋማት መሐል የአፍጋኒስታን የሰውነት ማጎልመሻና ስፖርት ጄኔራል ዳይሬክተር ቢሮ ይገኝበታል፡፡
‹በዘኪ ሞት ሐዘን ተሰምቶናል፡፡ ፈጣሪ ለቤተሰቡ፣ ለጓደኞቹና ለስፖርት ወዳጆች በሙሉ መጽናናትን ይስጥ› ብሏል ቢሮው ባወጣው የሐዘን መግለጫ፡፡
ሌሎችም በርካታ አፍጋኒስታናዊያን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ሐዘናቸውን በተመሳሳይ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የታሊባኖችን ወደ ካቡል መግባት ተከትሎ 4ሺህ 500 የአሜሪካ ወታደሮች ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን በጊዜያዊነት ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ይህም ዜጎቻቸውን በሰላም ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ከለላ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ ነው፡፡
ሆኖም በአስተርጓሚነትና በተለያዩ ሥራዎች ምዕራባዊያንን ሲያገለግሉ የነበሩ አፍጋናዊያን የታሊባንን የበቀል እርምጃ በመስጋት ለመሸሽ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ነበር፡፡
ታሊባኖች በአንጻሩ የጉዞ ሰነዶችን ያልያዙ አፍጋኒስታናዊያን ወደ አውሮፕላን ጣቢያው እንዳይገቡ ሲከላከሉ ነበር፡፡
የወጣቱ እግር ኳስ ተጫዋች ዛኪ አንዋር ካርዛይ አውሮፕላን ጣቢያ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ፣ በአውሮፕላኑ እንዴት እንደተንጠላጠለ፣ በምን ሁኔታ ሊወድቅ እንደቻለ እስካሁን የተብራራ መረጃ አልተገኘም፡፡












