ቱርክ የአፍጋኒስታንን አየር ማረፊያ ለመጠበቅ ፈቃደኝነቷን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቱርክ በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል የሚገኘውን አየር ማረፊያ በመቆጣጠር ጥበቃ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ገለጹ።
የአሜሪካ ወታደሮች ለሃያ ዓመታት ያህል ከቆዩባት አፍጋኒስታን መውጣታቸውን ተከትሎ ዋነኛው የመጓጓዣ ማዕከል የሆነውን አየር ማረፊያ ለመቆጣጠር ቱርክ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንቷ ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ገልጸዋል።
በአማጺያኑ ታሊባኖች ቁጥጥር ስር ከገባችው አፍጋኒስታን በአውሮፕላን ለመውጣት በርካታ ሰዎች እየተጠባበቁ ሲሆን በተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ይሰሩ ከነበሩት በተጨማሪ የአፍጋን ዜጎችም ወደ ሌሎች አገር ለመሄድ ጥረት እያደረጉ ነው።
በርካታ አገራትና ተቋማት በአፍጋኒስታን ውስጥ ያሉ ዜጎቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን በአውሮፕላን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የተለያዩ አገራት ከአፍጋኒስታን ጋር ያላቸውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ለመቀጠል ዋነኛ መተላለፊያ የሆነውን አየር ማረፊያ ክፍት አድርጎ ሥራውን እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚያስፈልግ እየተነገረ ነው።
ለዚህም ቱርክ አየር ማረፊያውን በመቆጣጠር ለማስተዳደር ፈቃደኛ መሆኗን በይፋ ገልጻለች።
ረቡዕ እለት በቴሌቪዥን ቀርበው የቱርክን ዕቅድ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ቀደም ሲል በነበረው ዕቅድ መሰረት የካቡል አውሮፕላን ማረፊያን ሥራውን እያከናወነ እንዲቀጥል ኃላፊነቱን ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"መላ አፍጋኒስታንን ታሊባን መቆጣጠሩን ተከትሎ አዲስ ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህም ካለው ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አዲስ ዕቅድ እያዘጋጀን ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ጨምረውም ከታሊባን መሪዎች ጋር ንግግር ለማድረግ ዝግጁ እንደነበሩ ገልጸዋል።
"ለየትኛውም አይነት ትብብር በራችን ክፍት ነው። የታሊባን መሪዎች ከቱርክ ጋር ከሚኖራቸው ግንኙነት አንጻር ጠንቃቆች ናቸው" ብለዋል።
ከሃያ ዓመት በፊት በአገሯ ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃትን ተከትሎ በወቅቱ የአፍጋኒስታን መሪዎች በነበሩት ታሊባኖች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በማካሄድ አሜሪካ አገሪቱን መቆጣጠሯ ይታወሳል።
ከሥልጣናቸው የተባረሩት ታሊባኖች ግን ፍልሚያውን ቀጥለው ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ድል ቀንቷቸው ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል ተመልሰው የመሪነት መንበሩን ከቀናት በፊት ተረክበዋል።












