አይኤምኤፍ ለአፍጋኒስታን የሚሰጠውን ገንዘብ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ለአፍጋኒስታን ሊሰጠው የነበረውን ገንዘብ ማገዱን አስታውቋል።
እርምጃው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ታሊባን ሃገሪቱን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ የመጣ ነው።
የአይኤምኤፍ ቃል አቀባይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአፍጋኒስታን መንግሥት እውቅና ላይ "በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ግልፅነት ባለመኖሩ" የተወሰነ ነው ብለዋል።
አይኤምኤፍ ከ370 ሚሊዮን ዶላር በላይ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ለአፍጋኒስታን ለመስጠት ወስኖ ነበር።
ይህ ገንዘብ በዓለም ላይ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ የአይኤምኤፍ ምላሽ አካል ነበር።
በመንግሥት ወደ ገንዘብ ሊለወጥ በሚችል ልዩ መብቶች (ኤስዲአር) ሃብቶች ውስጥ የሚገኘው የአይኤምኤፍ ክምችትም ታግዷል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "እንደ ሁልጊዜው አይኤምኤፍ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይመራል" ብለዋል።
ይህ የተገለጸው የአፍጋኒስታን መንግሥት በአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ያለው ማንኛውም ንብረት ለታሊባን እንደማይሰጥ ከባይደን ባለሥልጣናት አንዱ ለቢቢሲ ከተናገሩ በኋላ ነው።
በሌላ በኩል የኮንግረስ አባላት ለዩናይትድ ስቴትስ የግምጃ ቤት ጸሐፊ ጃኔት ዬለን በጻፉት ደብዳቤ ታሊባን በአሜሪካ የሚደገፍ ዕርዳታ እንደማያገኝ ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ቀደም ሲል የአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ኃላፊ አሜሪካ የአገሪቷን ገንዘብ እንዳታገኝ አግዳለች ብሏል። ሃገሪቱ 7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በአሜሪካ የፌዴራል ግምጃ ቤት ተይዞባታል።
በሳምንቱ መጨረሻ አገሪቱን ለቅቆ ለመውጣት የተገደዱት አጅማል አህመዲ በትዊተር ገጻቸው የዳ አፍጋኒስታን ባንክ አጠቃላይ ክምችት እስካለፈው ሳምንት ድረስ 9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር።
እንደ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ይህ ገንዘብ አብዛኛው እንደ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ቦንድ እና የወርቅ ባሉ ንብረቶች ተጠብቆ ይገኛል።
"ታሊባኖች አሁንም በዓለም አቀፍ ማዕቀብ ስር ስለሆኑ እንደዚህ ያሉ ንብረቶች እግድ እንደሚጣልባቸው ወይም ለታሊባን ተደራሽ እንደማይሆኑ ይጠበቃል" ሲሉ አህመዲ ተናግረዋል።
"ለታሊባን ተደራሽ የሆነው ገንዘብ ምናልባት ከአፍጋኒስታን አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ክምችት 0.1-0.2 በመቶ ያህሉ ሊሆን ይችላል። ብዙም አይደለም።" ብለዋል።
አህመዲ አክለውም የዋሽንግተን ዶላር እንዳይላክ መከልከሏ የአፍጋኒስታን ገንዘብ ምንዛሪ እንዲቀንስ እያደረገ ነው። የአፍጋኒስታን ገንዘብ የሆነው አፍጋኒ ከዶላር አንጻር ዝቅተኛ የምንዛሪ ምጣኔን አስመዝግቧል።
"ባንኮች ለደንበኞቻቸው ዶላር መስጠት እንደማይችሉ ይነግራሉ ብዬ አምናለሁ። ምክንያታቸው ደግሞ ማዕከላዊው ባንክ ለባንኮች ዶላር ስላልሰጠ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
"ይህ እውነት ነው። ገንዘቦች ስለተሰረቁ ወይም በመጋዘን ውስጥ ስለተያዙ አይደለም። ሁሉም ዶላር በታገዱ ዓለም አቀፍ ሂሳቦች ውስጥ ስለሆነ ነው" ብለዋል።
በሰኔ ወር አይኤምኤፍ ለአፍጋኒስታን የመጨረሻውን የብድር ክፍያ የሰጣት ሲሆን ይህም የጸደቀው ህዳር ላይ ነበር።
በዚሁ ወር ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "የታሊባን የገንዘብ ዋና ምንጮች የወንጀል ድርጊቶች እንደሆኑ" የሚገልጽ ዘገባ አሳትሟል።
ይህም "የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና የኦፒየም ምርት፣ ዝርፊያ፣ እገታ፣ የማዕድን ብዝበዛ እና ከሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ግብር በመሰብሰብ ነው።"
የዓለም ባንክም የሃገሪቱን በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ የሚደግፍ ሲሆን ከ 2002 ጀምሮ ለአፍጋኒስታን 5.3 ቢሊዮን ዶላር ሰጥቷል። የገንዘብ ድጋፉ ስላለበት ሁኔታ ላይ ቢቢሲ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
ገለልተኛው የገንዘብ አስተላላፊ ዌስተርን ዩኒየን በአፍጋኒስታን የገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎቶቹን እስከ ተጨማሪ ማስታወቂያ ድረስ አግዷል።
አይኤምኤፍ በብዙዎቹ አባላቱ እውቅና ባልሰጧቸው ሌሎች መንግስታት ላይም ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስዷል።
ከ50 በላይ አባል አገራት ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን የቬንዙዌላ ሕጋዊ መሪ አድርገው ባለመቀበላቸው ይህ እገዳ ተላልፏል። አይኤምኤፍ ወታደራዊው ጁንታ ሚያንማርን ከተቆጣጠረ በኋላ ክፍያዎችን ለሃገሪቱ አቁሟል።
አይኤምኤፍ ለ 190 አባል ሃገሮቹ 650 ቢሊዮን ዶላር የኤስዲአር ክፍያዎችን ሰኞ ያጠናቅቃል።












