ስደተኛው የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ሚሊዮን ዶላሮችን አሽሽተዋል መባሉን አስተባበሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቅርቡ ከአገራቸው የሸሹት የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት የነበሩት አሽረፍ ጋኒ ሚሊዮን ዶላሮችን ከካቡል ይዘው ወጥተዋል የሚለው ወሬ ‹መሰረተ ቢስና ሐሰተኛ› ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
አሽረፍ ጋኒ ትናንት በቪዲዮ ከተጠለሉበት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በሰጡት መግለጫ ከአገሪቱ በርካታ ገንዘብ መውሰዳቸው በስፋት እንደሚወራ ጠቅሰው ይህ ግን ፍጹም ሐሰት ነው ብለዋል፡፡
የታሊባንን ወደ ካቡል መገስገስ ተከትሎ ከአገራቸው የሸሹት የአፍጋኒሰታን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ የት አገር እንደሄዱ እስከ ትናንት ድረስ ሲያነጋግር ነበር፡፡
በመጨረሻ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አሽረፍ ጋኒ ከእኔ ዘንድ ናቸው ብላለች፡፡
አሽረፍ ጋኒ ካቡልን የለቀቁት ታሊባኖች ካቡል መግባታቸው እስደተሰማ በሰዓታት ውስጥ ባለፈው እሑድ ነበር፡፡
የኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሽረፍ ጋኒን እና ቤተሰባቸውን በእንግድነት የተቀበለው በሰብአዊነት ምክንያት ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
አገራቸውን በክፉ ጊዜ በዚያ ፍጥነት ጥለው መሄዳቸው አሽረፍ ጋኒን ለከፍተኛ ትችት ዳርጓቸው ቆይቷል፡፡
ትናንት ረቡዕ የቪዲዮ መግለጫ የሰጡት አሽረፍ ጋኒ ግን ‹እኔ ቶሎ አገሪቱን ጥዬ ባልሄድ ኖሮ በካቡል ደም ይፈስ ነበር› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"ለጊዜው ኢምሬትስ ነው ያለሁት፡፡ ደም መፋሰስ እንዲቆም በሚል ነው ወደዚህ የመጣሁት፡፡ አሁን ንግግር ጀምረናል፤ ወደ አፍጋኒስታን የምመለስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተነጋገርኩ ነው" ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
የ72 ዓመቱ ስደተኛው ፕሬዝዳንት አሽረፍ ጋኒ አገሪቱን ለታሊባን አስረክበው በዚያ ፍጥነት መሸሻቸው አፍጋኒስታናዊያንን ብቻ ሳይሆን ጆ ባይደንንም ያስገረመ ይመስላል፡፡
ባይደን ባለፈው ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አፍጋኒሰታናዊያን ለመዋጋትና ለመሞት የማይፈቅዱለትን ጦርነት የአሜሪካን ወታደሮች የሚሞቱት ምን በወጣቸው ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡
በፌስቡክ በቀጥታ ለሕዝብ በተላለፈው የአሽረፍ ጋኒ የትናንቱ መግለጫ ላይ ከካቡል የወጡበትን ሁኔታ የገለጹት ስደተኛው ፕሬዝዳንት እንዳብራሩት ከቤተ መንግሥት እንዲለቁ የተደረጉበትን ፍጥነት ‹ጠባቂዎቼ ጫማዬን እስካጠልቅ ድረስ እንኳ አልታገሱኝም›› ብለዋል፡፡
‹ፋታ አልነበረም፡፡ ከታሊባን ጋር የጥምረት መንግሥት እንዲኖር ለመደራደር ፈልጌ ነበር፡፡ ሆኖም ፋታ አልነበረም› ብለዋል አሽረፍ ጋኒ፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከአገራቸው ለሚሸሹ መሪዎች ከለላ ስትሰጥ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡
ኢምሬቶች ከዚህ ቀደም የፓኪስታኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት ቤናዘር ቡቶ በ1990ዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ ዱባይ የክፉ ጊዜ ቤታቸው እንድትሆን ፈቅደው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የተባቡሩት አረብ ኢምሬትስ የሌሎች አገሮች ፖለቲካ በፍጹም ወደ አፈሯ እንዲመጣ አትሻም ብሏል የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር፡፡
በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በርካታ ፓኪስታናዊያንና አፍጋኒስታናዊያን በሠራተኝነት ይኖራሉ፡፡
አሽረፍ ጋኒ ወደ ሥልጣን የመጡት በ2014 ሲሆን በየካቲት 2020 ደግሞ በድጋሚ ምርጫን አሸንፈው ነበር፡፡
ከዓመት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው አንድ ቃለ ምልልስ ታሊባን ወታደራዊ ድሎችን እያገኘ መሆኑ ያሳስባቸው እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ ‹ይህ ቬትናም አይደለም፡፡ መንግሥት ሊወድቅ አይችልም› ሲሉ ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡












