ለሃያ ዓመታት የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ እንዲፈታ ተመድ ጠየቀ

ስዊድናዊ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ

የፎቶው ባለመብት, ©EU/Belga/SCANPIX/KALLE AHLS

የምስሉ መግለጫ, ስዊድናዊ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ

ለሃያ ዓመታት ያህል ያለ ፍርድ የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በአስቸኳይ እንዲፈታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት አጣሪ እንዳሉት ዳዊት ይስሃቅ በባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ክስ አልተመሰረተበትም እንዲሁም ጠበቃውንም አግኝቶ አያውቅም።

የሰብዓዊ መብት አጣሪዋ ዳዊት ይስሃቅ በህይወት አለ የሚለው ጉዳይ ላይ ፍራቻ እንዳለ ገልፀው የኤርትራ ባለሥልጣናት የጋዜጠኛውን በህይወት መኖር ማስረጃ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።

ጋዜጠኛና ገጣሚው ዳዊት ይስሃቅ ነፃ ኤርትራን አገለግላለሁ በማለት ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶም የለውጥ ደጋፊ የሆነ ጋዜጣም አቋቁሞ ነበር።

የስዊድንና ኤርትራዊ ዜግነት ያለው ዳዊት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ነፃ ጋዜጦች ውስጥ አንዱን አቋቋመ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኤርትራ መንግሥት የግል ጋዜጦችን በመዝጋት የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት በጀመረው ዘመቻም ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ዳርጓል።

ጋዜጠኛው ዳዊት የፖለቲካ ተሃድሶን ከሚሹ ፖለቲከኞች የተላከ ግልፅ ደብዳቤ ካሳተመ በኋላም ነው ለእስር የተዳረገው።

ዳዊትን ጨምሮ በርካታ የግል ጋዜጣ አዘጋጆችም በጎሮጎሳውያኑ 2001 ለእስር ተዳረጉ።

ጋዜጠኛው ቤተሰቡን፣ ጠበቃውን እንዲሁም በተደጋጋሚ ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የስዊድን ተወካዮች እንዲያገኙት ጥያቄ ቢቀርብም ማንም ጎብኝቶት አያውቅም።

በህይወት እንዳለ የተጠረጠረው በጎሮጎሳውያኑ 2005 ሲሆን በእስር ላይ በፈታኝ ሁኔታ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከጋዜጠኛው እስር ጋር በተያያዘም ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤስኤፍ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ክሱን ስዊድን ለሚገኘው ዐቃቤ ሕህግ ከወራት በፊት አቅርቧል።

ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ ሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ቡድኑ ወንጅሏቸዋል።

ባለሥልጣናቱ ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲከፈትባቸው፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በማንገላታትና ያለበትንም ደብዛ በማጥፋት ክስ ይመሰርትባቸዋል ብሎም እንደሚያንም ቡድኑ በወቅቱ በድረ-ገፁ አስፍሯል።

በዓለም ላይ ለረዥም ዓመታት በእስር ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛ እንደሆነም ተገልጿል።

ቡድኑን በመወከል ክሱን ያቀረቡት ሁለት ስዊድናዊ ጠበቆች ሲሆኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ፣ የፍትህና የማስታወቂያ ሚኒስትሮችና ሌሎች አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተካትተውበታል።

"ባለሥልጣናቱ ምንም እንኳን ደረጃቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ዳዊትን ይስሃቅን አስረው ለሃያ ዓመታት እንዲበሰብስ ያደረጉት ግለሰቦች ለወንጀላቸው ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል" በማለት በክሱ ላይ ፊርማቸውን ካስቀመጡት አንዱ የሆኑት ጠበቃና የኖቤል የሰላም አሸናፊ ሽሪን ኢባዲ ናቸው።

"እነዚህ ግለሰቦች በፍፁም ማን አለብኝነት የፈለጉትን እንዲያደርጉና መክሰስ የሚችሉም አገራት ከተዋቸው ፍትህ በኤርትራ ሊሰፍን አይችልም" ብለዋል ጠበቃው።