አልቃኢዳ በአሜሪካ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ዕለትና ከዚያ በኋላ የሆነው ምን ነበር?

ሁለቱ መንትያ ህንጻዎች ጥቃት በደረሰባቸው ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ የታሪክ አጋጣሚ ብቻውን የዓለምን ፖለቲካ ሊገለባብጥ ይችላል። ለምሳሌ የመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃት።

ይህ ክስተት ከሃያ ዓመታት በፊት ነበር የሆነው። ለሁለት አሥርታት ግን የዓለምን ፖለቲካዊ መልክ ቀየረ።

ለመሆኑ የዛሬ 20 ዓመት ግድም ምን ነበር የሆነው? ክስተቱ ሲፈጸም ስንት ዓመታችሁ ነበር? የትስ ነበራችሁ? እንዴትስ ነበር የሰማችሁት?

የክስተቱን 20ኛ ዓመትና የታሊባኖችን ወደ ሥልጣን መመለስ ምክንያት አድርገን ይህን አሳዛኝ ክስተት በአጭሩ እንቃኛለን።

የሆነው ምን ነበር?

19 አሸባሪዎች በአራት ቡድን ተቧደኑና በአራት የተለያዩ የአሜሪካ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ውስጥ ተሳፈሩ።

ዓላማቸውም የአሜሪካንን ቁልፍ ተቋማትን በማውደም እንድትሽመደመድ ማድረግ ነበር።

አራቱ አውሮፕላኖች ወደ ምሥራቁ የአሜሪካ ክፍል የሚበሩ ነበሩ።

19ኙ ጠላፊዎች እነዚህን አውሮፕላኖች ወደ ተዋጊ አውሮፕላንነት መቀየር ነበር ትልማቸው።

የጦር አውሮፕላን በአሜሪካ ምድር ማብረር እንደማይችሉ ተረድተዋል። አዲሱ ሐሳብ ታዲያ ለምን ሰላማዊ አውሮፕላንን ወደ ሚሳኤልነት አንቀይረውም የሚል ሆነ።

ሐሳቡ እብደት ይመስላል። ይህንንም የእብደት ሕልማቸውን ግን በከፊልም ቢሆን አሳክተውታል።

ከመንገደኞች አውሮፕላንነት ወደ ሚሳኤልነት ተገደው የተቀየሩት አራቱ አውሮፕላኖች በዋሺንግተንና በኒውዮርክ ላይ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ጥቅም ላይ ዋሉ።

አራት ቁልፍ የአሜሪካን ሕንጻዎችን ዒላማ አደረጉ። አራቱን ቁልፍ የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶች ከአፈር ጋር ማመሳሰል ነበር ተልዕኳቸው።

በጥቃቱ ወቅት በስፍራው ነበሩ ሰዎች ሲሸሹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ወቅት በስፍራው ነበሩ ሰዎች ሲሸሹ

ያን ቀን በትክክል የሆው ምን ነበር?

በአገሬው አቆጣጠር ጠዋት 2፡46 ሲሆን ከአውሮፕላኖች አንዱ ተምዘግዝጎ ሰማይ ጠቀስ ከሚባሉት የዎርልድ ትሬድ ሴንተር መንትያ ሕንጻዎች አንዱን ጠርምሶ ገባ።

ሁለተኛው አውሮፕላን ደግሞ በደቡብ አቅጣጫ ካለው ለሌላኛው ሕንጻ የጋር ተላተመ። ይህም የሆነው በአገሬው አቆጣጠር ጠዋት ልክ 3፡03 ላይ ነበር።

ወዲያውኑ መንትያዎቹ ባለ 110 ፎቅ ሕንጻዎች እንደ ችቦ በእሳት ተንቦገቦጉ። ውቧ ኒውዮርክ በቅጽበት የፋብሪካ ጭስ ማውጫ መሰለች።

ሰዎች ከ110ኛ ፎቅ ጭምር እንደ አንዳች በራሪ ፍጡር ከመስኮት ዘለው ከአደጋው ለማምለጥ ሞከሩ። ከመፈጥፈጥ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም።

በዚያ ቅጽበት ምርጫው በእሳት መበላት ወይም ከ500 ሜትር ከፍታ መውደቅ ነበር።

ይህ ጉድ ለዓለም እንኳ በቅጡ ሳይዘገብ ሌላ ጉድ ተሰማ።

ጠዋት በአገሬው አቆጣጠር ልክ 3፡37 ሲሆን ደግሞ ሦስተኛው አውሮፕላን ወደ አሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን ተንደረደረ።

ፔንታገን የአሜሪካ ግዙፍ ወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤት ነው። ፔንታገንን ማውደም ማለት የአሜሪካንን ወታደራዊ ኃይል የማውደም ያህል እንደሆነ አሸባሪዎቹ የተረዱ ይመስላል።

የፔንታገን ግዙፉ መሥሪያ ቤት ከዋና ከተማዋ ዋሺንግተን ወጣ ብሎ ነው የሚገኘው።

ሦስተኛው አውሮፕላን ተምዘግዝጎ በዚህ በፔንታገን ላይ ቢወድቅም የሕንጻውን ምዕራባዊ ክንፉን ብቻ ነበር ማግኘት የቻለው።

የመንትያ ሕንጻዎቹ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመንትያ ሕንጻዎቹ ፍርስራሽ

አራተኛው አውሮፕላን ግን የት ገባ?

አራተኛው አውሮፕላን ዒላማ ያደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መቀመጫ የሆነውን ነጩን ቤተ መንግሥት እና ካፒቶል ሒልን ነበር።

አሸባሪዎቹ እንዳሰቡት ቢሳካላቸው ኖሮ ዋይት ሐውስ በቅጽበት ጽልመት በሆነ ነበር።

ሆኖም በዚህ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች ከአሸባሪዎቹ ጋር ተናነቁ። የሞት ሽረት ትግል አደረጉ። በዚህ የተነሳ አውሮፕላኑ ዒላማውን ሳተ።

ልክ በአገሬው አቆጣጠር 4፡03 ሲሆን ይህ አውሮፕላን በፔኒሲልቬኒያ አንድ ሜዳ ላይ ዒላማውን ስቶ ተከሰከሰ።

ስንት ሰዎች ሞቱ?

በድምሩ የሞቱት ንጹሐን 2977 ናቸው። በዚህ አሐዝ ውስጥ 19ኙ የአውሮፕላን ጠላፊዎች አልተካተቱም እንጂ እነሱም ሞተዋል።

ሟቾቹ አብዛኛዎቹ ኒውዮርክ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

በአራቱ አውሮፕላኖች ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ 246 ዜጎች በሙሉ አልቀዋል።

በመንትያዎቹ የኒውዮርክ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ላይ በነበሩት በ110 ወለሎች ውስጥ የነበሩ 2ሺህ 606 ዜጎች ሞተዋል።

በፔንታገን የነበሩ 125 ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል። ይህ ሁሉ ሲደመር ነው ወደ 3ሺህ ሰዎች በጥቃቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል የሚባለው።

የነፍስ አድን ሠራተኞች በጥቃቱ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Jose Jimenez / Getty Images

በዕድሜ ትንሿ ሟች ማን ናት?

ከሞቱት 3ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሁሉ በዕድሜ ትንሽ የተባለችው ሕጻን ክሪስቲን ሊ ሐንሰን ናት። ገና ሁለት ዓመቷ ነበር።

ከአራቱ አውሮፕላኖች በአንዱ ከአባቷ ፒተር እና ከእናቷ ሱ ጋር አብራ ነበረች።

ከሟቾቹ በዕድሜ ትልቁ የ82 ዓመቱ ሮበርት ኖርተን ናቸው። ከባለቤታቸው ጋር ከሠርግ እየተመለሱ ነበር።

110 ወለሎችን የሚረዝሙት መንትያ ንጻዎቹ ውስጥ ስንት ሰው ነበረ?

በኒውዮርክ መንትያ ሕንጻዎች ውስጥ የነበሩት ሰዎች ከሞቱት ሰዎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ብዙ ሕዝብ መትረፉን እንረዳለን።

የመጀመርያው አውሮፕላን ሕንጻውን ጠርምሶ ሲገባ በእነዚያ 110 ወለሎች ውስጥ 17ሺህ 400 ሰዎች ይርመሰመሱ ነበር።

አውሮፕላኑ ቦድሶ ከገባበት የሕንጻው ክፍል በላይ በነበሩ የሕንጻው ወለሎች ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንድም ሰው አልተረፈም።

ከደቡባዊው የሕንጻው ክፍል ግን 18 ሰዎች በተአምር መትረፍ ችለዋል።

ሟቾቹ ሁሉም አሜሪካዊያን አልነበሩም። የ77 አገራት ዜጎች ይገኙበታል።

በኒውዮርክ አደጋውን ተከትሎ ዜጎችን ለመርዳት ፈጥነው የደረሱ 441 የአደጋ ሠራተኞች ሞተዋል።

በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ሳይዘነጋ።

Tributes to the dead of 9-11

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, A collection of photos of the victims of 11 September 2001, in the 9/11 museum in New York

ጥቃት አድራሾቹ እነማን ናቸው?

ሁሉም የጽንፈኛ ኢስላም አራማጆች የነበሩ የአልቃኢዳ አባላት ናቸው።

አልቃኢዳ ይህን ጥቃት ቁጭ ብሎ የነደፈው በአፍጋኒስታን ምድር ነበር።

የዚህ ጥቃት መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ነው።

ለዚህ ጥቃት ያነሳሳውም አሜሪካ በሙስሊሙ ዓለም ጣልቃ እየገባች ግጭት ትፈጥራለች የሚል ነው።

በዚህ ጥቃት የተሳተፉት 19 የአልቃኢዳ አባላት ናቸው።

እነዚህ በሦስት ቡድን አምስት-አምስት ሆነው ተከፋፍለዋል።

ሦስተኛው ቡድን አራት አባላት ነበሩት።

ሦስተኛው ቡድን፣ አራት አባላት የተሳተፉበት አውሮፕላን ነጩን ቤተ መንግሥት ለመምታት ያለመውና በኋላም በተሳፋሪዎች ርብርብ ፔኒሴልቬኒያ ሜዳ ላይ የወደቀው ነው።

ከ19ኞቹ አሸባሪዎች ብዙዎቹ በትምህርት ብዙ ርቀት የሄዱ ናቸው።

አራቱ ደግሞ አውሮፕላን ማብረር የሚችሉ ፓይለቶች ነበሩ። አንዳንዶቹም የተማሩት በዚያው በአሜሪካ የበረራ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነበር።

ከ19ኙ አሸባሪዎች 15ቱ የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው ነበሩ። ሁለቱ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ አንዱ የግብፅ ዜጋ የነበረ ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ ሊባኖሳዊ ነበር።

የአሜሪካ ምላሽ ምን ሆነ?

ይህ ጥቃት ከደረሰ ወር እንኳ ሳይሞላ ጆርጅ ቡሽ አፍጋኒስታን እንድትወረር አደረጉ። እርምጃው ቢን ላደንን ለመያዝ ብሎም አልቃኢዳን ከምድር ለማጥፋት ነበር።

ሆኖም ቢን ላደንን ለመያዝ ሌላ 10 ዓመት አስፈልጎ ነበር። በመጨረሻም ቢን ላደን በአፍጋኒስታን ሳይሆን ፓኪስታን ውስጥ ከተደበቀበት ቤት በልዩ ኮማንዶዎች ተገደለ።

ይህን የመስከረም አንዱን ግዙፍ የሽብር ጥቃት አቀናብሯል የሚባለው ሰው ካሊድ ሼክ መሐመድ ይባላል።

በጎርጎሮሳዊያኑ በ2003 በፓኪስታን በቁጥጥር ሥር ውሎ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ። አሁንም ድረስ በጓንታሞ ቤይ በእስር ላይ ይገኛል። ለ20 ዓመት ፍርድ ሳያየገኝ እነሆ ፍርድ እየጠበቀ አለ።

አልቃኢዳ አሁንም ድረስ አለ። አሁንም በአፍጋኒስታን ውስጥ አባላት አሉት። ከሰሐራ በታች ባሉ አገራትም ይነስም ይብዛ ይንቀሳቀሳል።

የአሜሪካ ወታደሮች አሁን አፍጋኒስታንን መልቀቃቸው ምናልባት አልቃኢዳ ዳግም ያንሰራራ ይሆን የሚል ፍርሃትን ጭሯል።

የመስከረሙ ጥቃት ውርሶች

ይህ ዕለት የዋዛ አልነበረም። የዓለምን ፖለቲካ ፍጹም በሆነ መንገድ ነው የለወጠው።

በመላው ዓለም ፀረ ሽብር እንቅስቃሴ ተፋፋመ።

ምዕራባዊያን በዜጎቻቸው ላይ ጭምር ከፍተኛ ክትትል ማድረግ ጀመሩ። የድንበሮቻቸውን ቁጥጥር አጠበቁ። ስደተኞችን ለመቀበል አመነቱ።

የአውሮፕላን ጣቢያዎች ልዩ ጥበቃና ክትትል ይደረግላቸው ጀመር።

ሁለቱ መንትያ ሕንጻዎች የወደቁበትን ቦታ (ግራውን ዚሮ) ከፍርስራሽ ለማጽዳት ድፍን 8 ወራትን ወሰደ።

አሁን በአደጋው ለሞቱት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መታሰቢያና ቤተ መዘክርና በዚያ ስፍራ ይገኛል። ሁለቱ መንትያ ሕንጻዎች በተለየ ዲዛይን በድጋሚ ተገነቡ።

እንዲያውም ከቀድሞው ረዘም ተደርገው ነው የተገነቡት። አሁን ሽቅብ ወደ ላይ 541 ሜትር ይረዝማሉ።

ለመሆኑ ይህ የዓለምን ፖለቲካ ከሥር መሠረቱ የገለባበጠው የሽብር ጥቃት ከታሊባኖች መምጣት ጋር ተመልሶ ሊመጣ ይችላል?

ወይስ የዛሬ 20 ዓመት የነበረው ታሊባን በፖለቲካ በስሎ በአስተሳሰብ ተለውጦ ይሆን ካቡልን የተቆጣጠረው?