አልቃኢዳ ፡ የመስከረም አንዱ ጥቃት ሲታወስ፡ አልቃኢዳ የት ነው ያለው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
9/11 ተብሎ የሚጠራው ጥቃት እአአ መስከረም 11 ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአዲስ ዓመት በዓልን በሚያከብሩበት ዕለት በአሜሪካ መንትያ ህንጻዎች ላይ የሽብር ጥቃት ከተፈጸመ ዛሬ ልክ 19ኛ ዓመቱ ነው።
ጥቃቱን የፈጸመው በወቅቱ መቀመጫውን አፍጋኒስታን ያደረገው ጽንፈኛው ቡድን አል-ቃኢዳ ነበር።
በጥቃቱም አሜሪካውያን የማይረሱትን ጠባሳ እንዲያስተናግዱ ተገደዋል።
በሶሪያ የሚገኘው የአል-ቃኢዳ ክንፍ በተቀናቃኝ ኃይሎች ሰኔ ወር ላይ የተደመሰሰ ሲሆን በየመን የሚገኘው የአል-ቃኢዳ መሪ ደግሞ መሪው በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ከተገደ በኋላ ሌላ ሽንፈትን ገጥሞታል።
አል-ቃይዳ በሰሜን አፍሪካም ቢሆን ዋና መሪው በፈረንሳይ ወታደሮች ማሊ ውስጥ የተደገለ ሲሆን እስካሁንም ተተኪ አልተሰየመም።
በሌላ በኩል የአል ቃኢዳ መሪ አይማን አል ዛዋሂሪ ላለፉት ተከታታይ ወራት ድምጹ የጠፋ ሲሆን ምናልባትም ከኃላፊነቱ ተነስቶ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጭምጭምታ እየተሰማ ነው።
ማሊ ውስጥ በተካሄደ ዘመቻ በሰሜን አፍሪካ የአል-ቃኢዳ መሪ የነበረው አብድልማሊክ ድሮክዴል መገደሉን ይፋ ያደረገችው ፈረንሳይ ነበረች።
በአሜሪካ "አሸባሪ" ተብሎ ተፈርጆ ነበረው የቀድሞ የአል-ቃኢዳ መሪ የኦሳማ ቢን ላድን ልጅ ሃምዛ ቢን ላደን፣ አሜሪካ ባካሄደችው ዘመቻ መገደሉም ይታወሳል።
የአል-ቃኢዳ መሪዎች መገደል አል-ቃኢዳን ማዳከሙ እሙን ይሁን እንጂ፤ በአፍሪካ በማሊና ሶማሊያ ውስጥ አሁንም አል-ቃይዳ እንቅስቃሴ ያደርጋል።
ሶሪያ ውስጥ አል-ቃኢዳ በይፋ ባልተገለጸው ሁራስ ሰል ዲን ቅርጫፉ በኩል እዚህ ግባ የሚባል ነገር ማሳካት አልቻለም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በቀጠናው ያለው የሌሎች ጂሃዳዊ ቡድኖች ከፍተኛ ፉክክር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የትኞቹም የአል-ቃኢዳ መሪዎችና ከፍተኛ ኃላፊዎች በአሜሪካ ባለስልጣናት በጥብቅ ክትትል ስለሚደረግባቸው ነው።
በተጨማሪም አልቃኢዳ ሶሪያ ውስጥ ብዙም ተቀባይነት የለውም። ሶሪያውያን አል-ቃኢዳን እንደ ስጋትና ዓለም አቀፍ ተጽእኖ እና ጫና ይዞ እንደሚመጣ ቡድን ነው የሚያዩት።

የፎቶው ባለመብት, AQAP propaganda
ሁራስ አል ዲን በተቀናቃኝ ጂሃዳዊ ቡድን በተሰነዘረበት ከባድ ጥቃት ምክንያት ላለፉት ሁለት ተከታታይ ወራት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሲያድርግ አልታየም። ምናልባትም በአሜሪካ የአየር ድብደባ ሳይሞት እንዳልቀረም ተገምቷል።
የመን ውስጥ የቡድኑ ቅርጫፍ አል-ቃኢዳ በአረብ ባሕረ ሰላጤ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በአካበቢው እጅግ የሚፈራ ቡድን ነበር። ነገር ግን በያዝነው ዓመት በርካታ ጥቃቶችን ማስተናገዱና በተለያዩ ጦርነቶች መሸነፉ ተጽእኖ ፈጣሪነቱን እና ተቀባይነቱን አሳጥቶታል።
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ባደረሱት ጥቃት የዚሁ ቡድን መሪ የተገደለ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በማዕከላዊ ባይዳ ግዛት በሁቲ አማጺያን ተሸንፎ አካባቢውን እንዲለቅ ተገዷል።
በሰሜን አፍሪካም ቢሆን አል-ቃኢዳ አልጄሪያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ያደረገው ጥረት እምብዛም ፍሬ አላፈራለትም። በማሊ ደግሞ ጃማት ኑስራት አል ኢስላም ዋል ሙስሊሚን የሚባል የአል-ቃይዳ ክንፍ 2017 ላይ ተቋቁም የነበረ ሲሆን በቡርኪናፋሶ እና ኒጀርም ይንቀሳቀሳል።
ከአል-ቃኢዳ ጋር ወዳጅነት ካለውና በሶማሊያ መቀመጫውን ካደገረው አልሸባብ በመቀጠል ይሄው ቡድን በአፍሪካ ሰፋ ያለ ይዞታዎችን መቆጣጠር ችሏል።
ቡድኑም በዋነኛነት መከላከያ ኃይሎችን እና የውጭ አገራት ወታደሮችን ኢላማ በማድረግ ጠጥቃት ይፈጽማል። በተለይ ደግሞ የፈረንሳይ ወታደሮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃትን ይሰነዝራል።
በአሁኑ ጊዜ ለአል-ቃኢዳ እንደ አልሸባብ የሚያስፈራ ተቀናቃኝ የለውም። አልሸባብ ማዕካለዊና ደቡባዊ የሶማሊያ ከተሞችን ከመቆጣጠር ባለፈ ማስተዳደር ላይም ጭምር ይሳተፋል።
በሶማሊየም በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ ቀላልና ከባድ ጥቃቶችን ይሰነዝራል።
በርካታ የአል-ቃኢዳ ማዕከላዊ የአመራር አባላት በአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ድንበሮች አካባቢ ላለፉት ተከታታተይ ዓመታት በሰው አልባ አውሮፕላኖች በተሰነዘረባቸው ጥቃት ሞተዋል አልያም ሶሪያ ውስጥ በተከፈተባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል።
ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ በአሜሪካና ታሊባን መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትም ለውጥ እንዳመጣ ይታሰባል። በስምምነቱ መሰረት ታሊባን ማንኛውም አይነት የውጭ ጂሃዳዊ ቡድንን ላለመደገፍና ከለላ ላለመስጠት ተስማምቷል።
በሌላ በኩል አልቃኢዳ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን በመጠቀም አሜሪካውያን መንግሥታቸው ላይ አንዲነሱ ጥሪውን አቅርቧል። የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ ሊታደጋችሁ አልቻለም በማለትም መልዕክቱን አስታልፏል።
ነገር ግን አሜሪካውያን እድሜ ልካቸውን የማይረሱት ጥቃት ከሰነዘረባቸው ቡድን ጋር በአንድ ጎራ ይሰለፋሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።













