አርጀንቲና በሁለቱም ፆታ መጠራት ለማይፈልጉ አዲስ መታወቂያ አዘጋጀ

የአርጀንቲና ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

አርጀንቲና በሁለቱም ፆታ መገለፅ ለማይፈልጉ ዜጎቿ አዲስ ብሄራዊ መታወቂያ ስርዓት መዘርጋቷን ይፋ አድርጋለች።

እነዚህ ሰዎች በእንግሊዝኛው አጠራር 'ነን ባይነሪ' ይባላሉ።

በአርጀንቲና ህግ መሰረት አርጀንቲናዎች ራሳቸውን ከሁለቱም ፆታ ባገለለ መልኩ ማንነታቸውን የመግለፅ መብት አላቸው።

ነገር ግን ይህ በፓስፖርቶች እና በብሄራዊ ማንነት ሰነዶች (ዲኤንአይ) ተግባራዊ አይሆንም። በእነዚህ ማስረጃዎች ላይ አሁንም የተቀመጠው ወንድ ወይም ሴት የሚለው ምርጫ ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ፆታ መገለፅ የማይፈልጉና ለአዲስ መታወቂያ የሚያመለክቱ ሁሉ በፆታቸው 'ኤክስ' (x) የሚለውን መምረጥ ይችላሉ።

በፕሬዚዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ የወጣውን ድንጋጌ ተከትሎ አርጀንቲና ይህንን አዲስ ስርዓት የተቀበለች የመጀመሪያዋ የላቲን አሜሪካ ሀገር ናት።

በቦነስ አይረስ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ አዲሱን የመታወቂያ ካርዶች በአዲሱ "x" ይዘት ይፋ በማድረግ የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን ከአርጀንቲና የአገር ውስጥ ሚኒስትር እና ከሴቶች ፣ ከፆታ እና ከማንነት ሚኒስትር ጋር በመሆን አስረክበዋል።

ፈርናንዴዝ "ከወንድና ከሴት ማንነት በተጨማሪ ሌሎች ማንነቶች አሉ ፤ እነሱም መከበር አለባቸው" ብለዋል።

አክለውም "ሁላችንም በማንነታችን ስንቆምና ሰዎችም ስለ ፆታ ግድ የማይኖርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት" በማለት አስረድተዋል።

ፕሬዝዳንት ፈርናንዴዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አርጀንቲና፤ ካናዳን ፣ ህንድን እና ኒውዚላንድን ጨምሮ መደበኛ ማንነቶች ተብለው ከሚጠሩት ሁለት ፆታዎች በተለየ ይህንን ስርዓት አስቀድመው ከተቀበሉ በርካታ አገራት ጋር ተቀላቅላለች።

ፕሬዝዳንት ፈርናንዴዝ በአውሮፓውያኑ 2019 ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተራማጅ የሚባሉ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማምጣት ይታወቃሉ።

ባለፈው ዓመት የመሃል ግራው መንግሥታቸው ፅንስ ማቋረጥን ህጋዊ አድርጓል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመጣውን ጫና ለመቀነስና ለሕክምና አቅርቦቶች ክፍያ እና ለንግድ ድርጅቶች እፎይታ ለማገዝ የበለፀጉ ዜጎቿ በአንድ ጊዜ የሚከፈል ግብር ተግባራዊ አድርጋዋለች።