የ90 ዓመቷ አዛውንት በሁለት ዓይነት የኮቪድ ዝርያዎች ሞቱ

የኮቪድ ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ90 ዓመቷ አዛውንት በተለያዩ የኮሮና ዝርያዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ሰዎች በሁለት ዓይነት የኮቪድ-19 ተኅዋሲዎች ምክንያት ሊሞቱ እንደሚችሉ ሳይንቲስቶች እያስጠነቀቁ ነው።

የዕድሜ ባለፀጋዋ አልፋና ደልታ በተሰኙ ምንጫቸው ከደቡብ አፍሪካ ዩናይትድ ኪንግደም በሆኑ ዝርያዎች ምክንያት ነው የሞቱት።

ክትባት የወሰዱት የ90 ዓመቷ አዛውንት ባለፈው መጋቢት ነው ቤልጂዬም ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው።

ዶክተሮቿ እንደሚጠረጠሩት ሴትዬዋ ተኅዋሲዎቹን ያገኙት ከሁለት የተለያዩ ሰዎች ነው።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ምንም እንኳ ይህ የመጀመሪያው የተመዘገበ ክስተት ቢሆንም በሌሎች ቦታዎችም ብቅ ብቅ እያለ ነው።

የአውሮፓ ክሊኒካል ማይክሮባዮሎጂና ተላላፊ በሽታዎች ኮንግረስ ዘንድሮው በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ጉዳዩን አንስቶ እየተወያየ ነው።

ባለፈው ጥር ብራዚል ውስጥ ሁለት ሰዎች በሁለት የተለያዩ የኮቪድ-19 ዝርያዎች መያዛቸውን ይፋ አድርገው ነበር።

በሌላ በኩል የፓርቹጋል ተመራማሪዎች አንድ የ17 ዓመት ታዳጊ ከአንድ የኮቪድ ዝርያ እያገገመ በሌላ ዓይነት ኮቪድ ዝርያ መያዙን ተናግረው ነበር።

በሁለቱ በጣም አሳሳቢ በሚባሉት የኮሮና ዝርያዎች የተያዙት አዛውንት ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካላት ችግር እንደተስተዋለባቸው ተነግሯል።

የቤልጂዬሙ ኦኤልቪ ሆስፒታል ዋና ተመራማሪዋ ዶክተር አን ቫንኪርበርገን ሁለቱ ዝርያዎች ሴትዬዋ በታመሙ ወቅት ቤልጂዬም ገብተው ነበር ይላሉ።

"ብቻቸውን ነበር የሚኖሩት። ነገር ግን በርካታ ሰዎች ሊያግዟቸው ይመጡ ነበር" ብለዋል ዶክተሯ።

የሁለቱ ዝርያዎች መደባለቅ ሴትዬዋ በፍጥነት ጤናቸው እንዲቃወስ ያድርግ አያድርግ ገና ጥናት ያሻዋል ይላሉ ዶክተር አን።

ቫይረሶች ከሰው ሰው ሲዛመቱ ዝግመተ ለውጣቸው ይቀያየራል። ይህም አዲስ ዓይነት ዝርያ ይፈጥራል።

ኮቪድም ይህን ዝግመተ ለውጥ ተከትሎ ቅርፁን እየቀያየረ በአዲስ ዝርያ እየመጣ ነው። አንዳንዶቹ ዝርያዎች የሰውነት መከላከል አቅምንና ክትባትን መገዳደር ጀምረዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በፍጥነት እየተዛመተ ያለው ደልታ የተሰኘው ዝርያ ነው።

ነገር ግን ተመራማሪዎች አሁን በመሰጠት ላይ ያሉ ክትባቶች እኒህን ዝርያዎች የመከላከል አቅማቸው አስተማማኝ ነው ይላሉ።

ሳይንቲስቶች አሁንም ኮቪድን በመከላከል የተሻለ አቅም ያለው ክትባት ለማምረት ደፋ ቀና እያሉ ነው።