የሄይቲውን ፕሬዝደንት የገደሉት ቅጥረኛ የሆኑ የውጭ ዜጎች ናቸው ተባለ

የአገሪቱ የገዳዩ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸውን ግለሰቦችን እና ከቡድኑ የተያዙ ናቸው ያላቸውን ጦር መሳሪያዎች ለመገናኛ ብዙሃን አሳይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአገሪቱ የገዳዩ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸውን ግለሰቦችን እና ከቡድኑ የተያዙ ናቸው ያላቸውን ጦር መሳሪያዎች ለመገናኛ ብዙሃን አሳይቷል።

የሄይቲው ፕሬዝደንት ጆቨኔል ሞይዝን የገደሉት 28 አባላት ያሉት ቅጥረኛ የገዳዮች ቡድን ነው ሲል ፖሊስ አስታወቀ።

ከእነዚህ መካከል ሃያ ስድስቱ ኮለምቢያዊያን ናቸው ሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሄይቲያዊያን ናቸው ሲሉ የፖሊስ አለቃ ሌዎን ቻርልስ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ሁለቱ አሜሪካዊያንን ጨምሮ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ስምንቱ ደግሞ እየታሰሱ እንደሆነ ተሰምቷል።

በሕይወት ካሉት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ዋና መዲናዋ ፓርቶፕሪንስ ውስጥ ከፖሊስ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ የሞቱ እንዳሉም ታውቋል።

ባለፈው ረቡዕ ነው የታጠቁ ሰዎች ወደ ፕሬዝደንቱ መኖሪያ ቤት ገብተው ጥቃት የፈፀሙት።

በጥቃቱ ፕሬዝደንት ጆቨኔል ሞይዝ ሲገደሉ ሚስታቸው ማርቲን ደግሞ ቆስለው ፍሎሪዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለሕክምና ተወስደው አሁን መልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል።

ጥቃቱን ማን እንዳቀደውና ዓላማው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ነገር ግን ተጠባባቂው ፕሬዝደንት ክሎውድ ጆሴፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የ53 ዓመቱ ፕሬዝደንት ሰለባ የሆኑት "ሥልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ መሆኗን" መቃወም በመጀመራቸው ሳይሆን አይቀርም።

ሐሙስ ዕለት ፖሊስ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል የተወሰኑትን ከእነ ጦር መሣሪያቸውና ፖስፖርታቸው ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጓል።

"የተቀሩትን አራት ሰርጎ ገቦች ለመያዝ ምርመራችንን እንዲሁም የፍለጋ መላችንን እናጠናክራለን" ብለዋል ቻርልስ።

"በጣም የተደራጀ ኮማንዶ ነው። ከስድስት በላይ መኪናዎችና በርካታ ቁሳቁሶች ያለው ነው" ያሉት ደግሞ የሄይቲ ምርጫ ሚኒስትር ማቲያስ ፒዬር ናቸው።

ኮለምቢያ ቢያንስ ስድስቱ የገዳይ ቡድን አባላት ጡረታ የወጡ ወታደሮቼ ሳይሆኑ አይቀሩም ብላለች። ሃገሪቱ ከሄይቲ ጋር ለመተባበር መወሰኗን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ዜጎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ማጣራት እንዳልቻለ አስታውቋል።

መርማሪዎች አሁንም ከጥቃቱ ጀርባ ያሉትን ሰዎች እየፈለጉ ነው።

የፕሬዝደንቱ ግድያ በአህጉረ አሜሪካ ድህነት የናጣት ሃገር በምትባለው ሄይቲ ተቃውሞ እንዲነሳ አድርጓል።

ይህን ተከትሎ የ15 ቀናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሄይቲ ታውጇል።

ምንም እንኳ የሄይቲ ሕገ-መንግሥት ፕሬዝደንቱ ከሞቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ይሾማሉ ቢልም ዳኛው በቅርቡ በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በኋላ ማሻሻያዎች ተደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይምሩ የሚል ሐሳብ መጥቷል። አሪዬል ሄንሪ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቢሾሙም እስካሁን ቃለ መሐላ አልፈፀሙም።

የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ ምክትሉ ጆሴፍ በተጠባባቂ ፕሬዝደንትነታቸው እስከ ምርጫ ድረስ መቆየት አለባቸው ይላል።

11 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሄይቲ 59 በመቶ ሕዝቧ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ።

የተፈጥሮ አደጋ የማያጣት ሄይቲ በፈረንጆቹ 2010 በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ 200 ሺህ ዜጎቿን አጥታለች።